የዮርዳኖሱ ልዑል በቁም አስር ላይ እንደሆነ ተናገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የዮርዳኖስ ልዑል አልጋ ወራሽ የአገሪቱ ንጉሥ በተቺዎቻቸው ላይ ከሚወስዱት እርምጃ ጋር በተያያዘ በቁም እስር ላይ እንደሆነ ተናገረ።
የዮርዳኖሱ ንጉሥ አብዱላህ ወንድም የሆነው ልዑል ሐምዛ ቢን ሁሴን በጠበቃው አማካይነት ለቢቢሲ በላከው ቪዲዮ ላይ የአገሪቱን መሪ በሙስና፣ በብቃት ማነስና ጥቃት በመፈጸም ይከስሳል።
ይህ የልዑሉ መልዕክት የወጣው መፈንቅለ መንግሥት ለመፈጸም ሴራ እየተጠነሰሰ ነበር ከሚል ውንጀላ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኙ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ ነው።
ቀደም ሲል የዮርዳኖስ ጦር ሠራዊት ልዑል ሐምዛ በቁም እስር ላይ እንዳልሆነ ገልጾ ነበር።
ነገር ግን ልዑሉ የዮርዳኖስን "ደኅንነትና መረጋጋት" ኢላማ ለማድረግ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ተግባራትን ከመፈጸም እንዲቆጠብ ታዝዞ እንደነበር ሠራዊቱ ገልጿል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው ልዑሉ ድጋፍን አግኝቶበታል የተባለውን የተለያዩ ጎሳ መሪዎችን በመጎብኘት ከተወያየ በኋላ ነው።
ልዑል ሐምዛ ከተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ውስጥ እንደሌለበትና ምንም አይነት ድርጊት ውስጥም እንደሌለበት አስተባብሏል።
ልዑል ሐምዛ የቀድሞው ንጉሥ ታላቅ ልጅ ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ውስጥ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ውስጥ አገልግሏል።
ከሃያ ዓመታት በፊት አባቱ ንጉሥ ሁሴን በህይወት ሳሉ ልዑል አልጋ ወራሽ ብለው ሰይመውት የነበረ ሲሆን ንጉሡ ባረፉበት ጊዜ ገና ልጅና ልምድ አላዳበረም በሚል በአባት በኩል ወንድሙ የሆነው አብዱላህ ንግሥናውን ተረክቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጽንና ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ የአካባቢው ተሰሚ አገራት ድጋፋቸውን ለንጉሥ አብዱላህ ገልጸዋል።
በአይኤስ ላይ እያካሄደች ላለው ዘመቻ አጋሯ የሆነችው አሜሪካም ንጉሡን በአካባቢው ቁልፍ ወዳጇ እንደሆኑ በመግለጽ ሙሉ ድጋፏን እንደምትሰጣቸው አመልክታለች።
ዮርዳኖስ ያላት ውስን የተፈጥሮ ሀብት ሲሆን በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ምጣኔ ሀብቷ ክፉኛ ተጎድቷል። በተጨማሪም በሶሪያ በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች እያስተናገደች ትገኛለች።
ልዑሉ ቅዳሜ በላከው ቪዲዮ ላይ ተሳታፊ በነበረበት ስብሰባ ላይ በመንግሥት ወይም በንጉሡ ላይ በሰነዘረው ትችት ምክንያት ከቤት መውጣትና ከሰዎች ጋር መገናኘት እንደማይችል እንደተነገረው ገልጿል።
ጨምሮም "ባለፉት ከ15 አስከ 20ዓመታት ለነበሩትና እየተባባሱ ለሄዱት በመንግሥት ውስጥ ለተፈጠረው የአስተዳደር ችግር፣ ለሙስናና ለብቃት ማነስ እንዲሁም ሕዝቡ በአገሪቱ ተቋማት ላይ እምነት ለማጣቱ ተጠያቂ አይደለሁም" ብሏል።
"በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው ሃሳቡን በመግለጹ መሳለቂያ ሊሆን፣ ሊታሰር፣ ሊጠቃና ዛቻ ሊደርስበት ከሚችልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።"
በዮርዳኖስ ውስጥ በፖለቲካው ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ባሉ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር የተለመደ አይደለም።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ኃያሉ የአገሪቱ የደኅንነት ተቋም ተጨማሪ ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን ከሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ቡድኖች ትችቶች ይሰነዘሩበታል።












