ተፈጸመ ስለተባለው ግድያ የኢትዮጵያ መንግሥት ምርመራ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

ትግራይ ውስጥ ማኅበረ ዴጎ በተባለ ስፍራ ተፈጽሟል የተባለውን ግድያን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ምርመራ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።
ይህ የተነገረው ትግራይ ውስጥ በኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ሰዎች መገደላቸውን በተመለከተ ለወጣው ዘገባ በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምላሽ በሰጠበት መግለጫ ነው።
ኤምባሲው ላለፉት ሳምንታት በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሲዘዋወር የቆየውንና አሁን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ርዕስ ስለሆነው ትግራይ ማኅበረ ዴጎ በሚባል ቦታላይ ተፈጽሟል የተባለውን ጭፍጨፋ የሚያሳየውን የሚረብሽ ቪዲዮ እንደተመለከተው ገልጿል።
የቢቢሲ 'አፍሪካ አይ' ፕሮግራምም በዚሁ ቪዲዮ ላይ ባደረገው ምርመራ ግድያው በኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ማግኘቱንና በዚህም ቢያንስ 15 ሰዎች የተገደሉበትን ትክክለኛው ቦታ ለመለየት መቻሉን ዘግቦ ነበር።
ኤምባሲው በመግለጫው ላይ በንጹሃን ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸምን ጥቃትም ሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ እንደሚያወግዝ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በተልዕኮ ላይ ያሉ ወታደሮችን ጨምሮ ማንም ሰው ከሕግ በላይ አለመሆኑን ያመለከተው የኤምባሲው መግለጫ፤ መንግሥት የተፈጸሙ በደሎችን በጥልቀት ለመመርመር ቁርጠኛ መሆኑንና ማስታወቁን አስታውሷል።
ከዚህም አኳያ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የተባሉትን የወንጀል ድርጊቶችን የፈጸሙትን ተጠያቂ ለማድረግ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከፌደራል ፖሊስ የተወጣጣ ልዩ ግብረ ኃይል ባለፉት ሳምንታት ጉዳዩን ከስፍራው ሆኖ ለማጣራት ወደ ትግራይ መሰማራቱን ገልጿል።
ኤምባሲው አክሎም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመሆን በትግራይ ተፈጽመዋል የተባሉ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ እንደሚያደርግና ውጤቱንም ይፋ ይደረጋል ብሏል።
የእነዚህ ምርመራዎች ውጤትም የጥፋቱን ፈጻሚዎች ለሕግ ለማቅረብና ትግራይ ውስጥ ተፈጸሙ ለተባሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና ወንጀሎች ምላሽ ለመስጠት መንግሥትን እንደሚያስችል አመልክቷል።
ኤምባሲው ለማየት የሚረብሸውን ቪዲዮ በተመለከተም ተፈጽሟል ስለተባሉት ወንጀሎች ምርመራ እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት መገናኛ ብዙሃንና ሕዝቡ ግምት ላይ የተመሰረት ሃሳብ ከመሰንዘር እንዲቆጠቡ ጠይቋል።
የታጠቁና የወታደር የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ያልታጠቁ ወንዶችን ከአንድ የገደል አፋፍ ላይ በመውሰድ አንዳንዶቹን ላይ በቅርብ ርቀት በመተኮስ አስከሬኖችን ወደ ገደል ገፍተው ሲጨምሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታይቶ ነበር።
ቢቢሲ ይህ ድርጊት የተፈጸመው የኢትዮጵያ ሠራዊት የህወሓት ኃይሎችን እየተዋጋ ባለበት ትግራይ ክልል ውስጥ ማኅበረ ዴጎ ከተባለች ከተማ አቅራቢያ መሆኑን አረጋግጧል።
ቀደም ሲል ቢቢሲ ያገኛቸውን ማስረጃዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት በማቅረብ ምላሽ የጠይቆ የነበረ ሲሆን መንግሥት "በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ነገሮችና ክሶች እንደ ማስረጃ ሊወሰዱ አይችሉም" በማለት "ገለልተኛ ምርመራዎችን ለማካሄድ የትግራይ ክልል ክፍት ነው" ሲል ምላሽ ሰጥቶ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንደተናገሩት፣ ትግራይ ውስጥ በኢትዮጵያ ሠራዊት ተፈጸሙ ስለተባሉት ጥፋቶች አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ አጥፊዎች በሕግ እንደሚጠየቁ መናገራቸው ይታወሳል።
ትግራይ ውስጥ ግጭቱ የተቀሰቀሰው የህወሓት ኃይሎች በመንግሥት ጦር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር።
ህወሓትም የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ በመቃወም "ትግሉን እንደሚቀጥል" ገልጾ ነበር።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዳለው ግጭቱ አስካሁን ድረስ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ እንዲፈናቀሉ ያደረገ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል።
ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ወቅት በተለያዩ የግጭቱ ተሳታፊዎች ከባድ የመብት ጥሰቶችና ጥቃቶች እንደተፈጸሙ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የሰብአዊ መብት ተቋማት ሪፖርት ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተና ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ተፈጸሙ ስለተባሉት የመብት ጥሰቶች ምርመራ ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።















