በታይዋን በባቡር ላይ በደረሰ አደጋ በርካቶች መሞታቸው ተገለፀ

በታይዋን 500 ሰዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ባቡር ላይ በደረሰ አደጋ 41 ሰዎች ሲሞቱ እስካሁን ድረስ፣ በመተላለፊያ ዋሻ ውስጥ 200 ሰዎች ታግተው እንደሚገኙ ተገለፀ።

የነፍስ አድን ሰራተኞች መተላለፊያ ውስጥ ከተቀረቀረው የባቡር ፉርጎ ሰዎችን ለማውጣት እየጣሩ ሲሆን በርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።

ባለ ስምንት ፉርጎው ባቡር አደጋው ያጋጠመው ሀዲዱ ላይ ተንሸራቶ የቆመ የግንባታ መኪና ጋር በመጋጨቱ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

ባቡሩ ከታይዋን ዋና ከተማ ታይፔይ፣ ወደ ታይቱንግ ዓመታዊ በዓል ለማክበር የሚሄዱ ሰዎችን ጭኖ በር።

ባቡሩ ሙሉ ስለነበር የቆሙ ተሳፋሪዎች ነበሩ ተብሏል።

ይህ 408 የሚል መለያ ቁጥር የተሰጠው የባቡር መስመር በሰዓት 130 ኪሎሜትር የሚጓዝ ሲሆን ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ተብሏል።

የአገሪቷ ብሔራዊ እሳት አደጋ ኤጀንሲ ባቡሩ 409 ሰዎችን ማሳፈሩን ገልጾ 41 ሰዎች ሲሞቱ 60 የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል አስታውቋል።

የባቡሩ የመጨረሻ ፉርጎ ላይ የነበሩ ተሳፋሪዎች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው የወጡ ሲሆን፣ ከመጀመሪያዎቹ አራት ፉርጎዎች የታገቱ ሰዎችን ለማውጣት በሚደረገው ጥረት 200 ያህሉ አሁንም ታግተው እንደሚገኙ ታውቋል።

አደጋው የደረሰበት ባቡር ከታይዋን ዋና ከተማ የተነሳ ሲሆን በውስጡም በአገሪቱ በድምቀት የሚከበረው ዓመታዊ በዓል ለማክበር የሚሄዱ ሰዎች ማሳፈሩ ተገልጿል።

ይህ ዓመታዊ በዓል የሚከበርበት ቀን የተቃረበ ሲሆን ወቅቱም በርካታ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንደሚበዛበት ተገልጿል።

በዚህ ወቅት ታይዋናውያን ወደ ወዳጅ ዘመዶቻቸው የመቃብር ስፍራ በመሄድ ፀሎት ያደርሳሉ።

ባቡሩ ሞልቶ ስለነበር በርካታ ተሳፋሪዎች ቆመው እንደነበር ተገልጿል።

ካልተጎዳው የባቡሩ ፉርጎ የወጡ ሰዎች እቃቸውን በመያዝ ሲሄዱ ታይተዋል።

ከተሳፋሪዎቹ መካከል ለታይዋን መገናኛ ብዙሃን ማንነቷን ያልገለፀች መንገደኛ ያየችውን ስትናገር "ድንገት የተፈጠረ መንገጫገጭ ተሰማ እና ወለሉ ላይ ወደቅኩ" ብላለች።

አክላም "መስኮቱን ሰብረን ወደ ጣሪያው በመውጣት ተርፈናል"

እንደ ታይዋን ፕሬዝዳንት ሳይ ኢንግ ዌን ከሆነ አሁንም በርካታ ሰዎች የባቡር ፉርጎው ውስጥ መውጫ አጥተው ይገኛሉ።

"ዛሬ ማለዳ በሁዋሌን መተላለፊያ ዋሻ አደጋ አጋጥሟል" ብለዋል በመግለጫቸው።

አክለውም "በአደጋው ለተጎዱ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ የሚሰጡ ሠራተኞች በስፍራው ይገኛሉ። ቅድሚያ በባቡር ፉርጎው ውስጥ ላሉ ይሰጣል" ብለዋል።

ሮይተርስ የእሳት አደጋ ቢሮውን በመጥቀስ ከአራቱ የባቡር ፉርጎዎች 100 ሰዎች መውጣታቸውን ዘግቧል።