የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እንዴት በፍጥነት ሊታረም ቻለ?

የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ከዚህ ቀደም ባልነበረ ፍጥነት ከሦሰት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አርሞ ውጤቱን በዚህ ሳምንት አስታውቋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት የፈተናውን ውጤት ለማሳወቅ ወራት ይጠይቅ የነበረ ሲሆን የአሁኑ ከየትኛውም ጊዜ በፍጥነት ተጠናቅቋል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚለው ብዙዎች ጥያቄ ነው።

ቢቢሲ የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዴላሞ ኦቶሬን (ዶ/ር) ይህንን ጠይቋቸው ሲመልሱ፤ ፈተናው መጋቢት 2/2013 ዓ.ም መጠናቀቁን አስታውሰው ከመጋቢት 3/2013 ዓ.ም ጀምሮ መረከብ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

በቅድሚያም 20 ሺህ አካባቢ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ተፈታኞችን እርማት መጋቢት 4/2013 ዓ.ም ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።

አጠቀላይ ፈተና የማረሙን ሂደት በአንድ ሳምንት ማጠናቀቃቸው የሚናገሩት ኃላፊው፣ ቀሪው ሥራ መረጃ ማጥራት ስለነበር እርሱን ሲሰሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

ስለሚጠቀሙበት ቴክኖሎጂም ሲናገሩም "የብሪቲሽ ዲ አር ኤስ ቴክኖሎጂን ነው፤ አዲስ የተቀየረ ቴክኖሎጂ የለም" ብለዋል።

ማሽኑ በ24 ሰዓት ውስጥ በአማካኝ 420 ሺህ ፈተና ወረቀቶችን ያርማል ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህ ቴክኖሎጂ የእያንዳንዱን ተፈታኝ መልስ መስጫ ወረቀት ስካን በማድረግ ወደ ኮምፒውተር እንደሚያስገባ በመግለጽ ይህንንም ለማድረግ 24 ማሽኖች እንዳሉ አብራርተዋል።

ፈተናው በፈረቃ ለ24 ሰዓት ሲታረም መቆየቱን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ተማሪዎች በፈተና መራዘም ምክንያት በስነልቦና በመጎዳታቸው ይህንን ለማካካስ ቶሎ ውጤቱን ለመግለጽ ጠንክረው መስራታቸውን ይናገራሉ።

ፈተናውን በፍጥነት አርሞ ለማጠናቀቅ ሶስት ነገሮች ምክንያት ሆነዋል ያሉት ኃላፊው የመጀመሪያው ፈተናው በሰላም መጠናቀቁ መሆኑን ያስረዳሉ።

በሰላም ባይጠናቀቅ ኖሮ የሚጣራ ጉዳይ፣ በፖሊስ እጅ የተያዙ ጉዳዮች፣ የእርማት ጊዜውን እንዲዘገይ ያደርገዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

ሁለተኛው የሰዓት አጠቃቀም ነው በማለት፣ በፈረቃ 24 ሰዓት መታረሙን ያስታውሳሉ። ይህም ፈተናውን አርሞ ለማጠናቀቅ የሚወስደውን ጊዜ ለማጠናቀቅ አጭር ጊዜ መውሰዱን ይናገራሉ።

ሶስተኛው ስራውን ለመምራት የተጠቀምንበት የአደረጃጃት እና አመራር ስርዓት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እነዚህ ሶስቱ ጉዳዮች ተቀናጅተው እንደተባለው በፍጥነት እንዲያልቅ አድርጓል ብለዋል።

በእርማት ወቅት ማሽኑ ስህተት የሚሰራበት እድል በጣም አነስተኛ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎች ቅሬታቸውን በማቅረብ እንደሚስተናገዱ ተናግረዋል።

ተማሪዎች ቅሬታ በሚያቀርቡበት ወቅት መከተል ያለባቸው ነገሮችን ሲያስረዱም በያሉበት ኦንላየን ሆነው የተዘጋጀውን ቅጽ መሞላት አልያም በአካል በጽሑፍ ማቅረብ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ካለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተየያዘ ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎች በኦንላየን እንዲያስገቡ ይመክራሉ።

የተማሪዎችን ቅሬታ ለመመልከት ብቻ የተቋቋመ ኮሚቴ እንዳለ የሚናገሩት የኤጀንሲው ዳይሬክተር በፍጥነት ምላሽ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

ቅሬታውን በፍጥነት ምላሽ የሚሰጥበት ምክንያት ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ነጥብ ከመገለፁ በፊት ለማስታወቅ ስለሚሰራ አእንደሆነም አብራርተዋል።

አንድ ተማሪ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ከተነገረ በኋላ ቅሬታውን ቢያቀርብ ጉዳዩ ታይቶ የሚደረግ ማስተካካያ ካለ እንደሚሰራ ጨምረው ገልፀዋል።

የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የ2012ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በተመዝጋቢ፣ በተፈታኝም እንዲሁም በውጤትም ደረጃ ከፍተኛ መሆኑ አስታውቋል።

እንደ ኤጀንሲው መረጃ ከሆነ ከ350ሺ ተማሪዎች በላይ ተመዝግበው፤ ተፈትነው ውጤታቸውን ማወቅ ችለዋል።

ኤጀንሲው የተፈታኞች ቁጥር ከሌሎች ዓመታት በተለየ ከፍ ያለ ነው ማለቱን ተከትሎ በዚህ በኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ እንዴት ሊጨምር ቻለ በማለት የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዳይሬክተር

ይህ መረጃ ተያይዞ የሚመጣው 10ኛ ክፍል ለመሰናዶ መግቢያ ተፈትነው ካለፉ ጋር መሆኑን ያስረዳሉ።

የእነዚህ የመሰናዶ መግቢያ ፈተና ወስደው ባለፈው ዓመት ለመፈተን ሲጠባበቁ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥር ሲታይ መቀነስ እንደማያሳይ አብራርተዋል።

ዘንድሮ ፈተናውን የወሰዱ 350ሺህ ተማሪዎች መፈተን የነበረባቸው ባለፈው ዓመት ቢሆንም የኮቨድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመከሰቱ ወደ 2013 ዓም እንዲገፋ አድርጎታል።

የኤጀንሲ ዳይሬክተር ለሆኑት ዴላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) ዘንድሮ ስላጋጠመ ኩረጃ ጥያቄ ቀርቦላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ኩረጃን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

ፈተናው በሚሰጥበት ወቅት በአንዳንድ ክልሎች ተማሪዎች ወደ መፈተኛ ክፍል ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው መግባት እንደሌለባቸው እየታወቀ ይዘው መግባታቸውን ገልፀዋል።

ይህ ያጋጠመው የመጀመሪያዎቹ ፈተናዎች፣ ሒሳብ እና እንግሊዘኛ ፈተናዎች ከተጠናቀቁ በኋላ እና አፕቲትዩድ እየተሰጠ በነበረበት ወቅት መሆኑንም ያስታውሳሉ።

ኩረጃው ያጋጠመው ተማሪዎች ወደ መፈተኛ ክፍል ከገቡ በኋላ በመሆኑ ለመቆጣጠር መቻሉን የገለፁት ኃላፊው ከዚህ ቀደም አጋጥሞ አንደነበረው ያለ አስቀድሞ ስርቆት አለመኖርን አስረድተዋል።

በዚህም የተነሳ በፈተና ክፍል ውስጥ የተሰጣቸውን ፈተና ወረቀት ፎቶ በማንሳት ውጪ ላለ ሰው በቴሌግራም ልኮ ማሰራት እንዳጋጠመ ይናገራሉ።

በዚህ ዓመት በዚህ መንገድ የኮረጁ ከ20 በላይ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ውጤታቸው ሲሰረዝ፣ 10 ያህል ተፈታኞች ደግሞ አንድ ትምህርት ሲኮርጁ በመገኘታቸው በዚያ ትምህርት ውጤት እንዳያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል።