ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይኪ የሰው ደም ያረፈበት "የሰይጣን ጫማ" ላይ የመሰረተውን ክስ አሸነፈ
ናይኪ አጨቃጫቂ በሆነው እና እውነተኛ የሰው ደም ጠብታ በሶሉ ላይ መያዙ በተነገረለት የኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) "የሰይጣን ጫማ" ምርት ላይ የመሰረተውን ክስ አሸነፈ።
1,018 ዶላር ዋጋ የተቆረጠለት ይህ ጫማ የተሰራው ከናይኪ ኤይር ማክስ 97 ጋር ተመሳስሎ ሲሆን የተገለበጠ መስቀል፣ ባለአምስት ጫፍ ኮከብ እና የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ከቁጥር 18 የሚል ጥቅስ ሰፍሮበታል።
አድናቂዎቹ ሚስቺፍ በማለት የሚጠሩት የብሩክሊን የጥበብ ሥራዎች ሰብሳቢ ይህንን ጫማ ያመረተው ከራፐሩ ሊል ናስ ኤክስ ጋር በመጣመር ነው።
666 ጫማዎች ብቻ ማምረቱን የገለፀው ኩባንያው የተወሰነው ለገዙት ሰዎች ተልኳል።
ናይኪ የንግድ ምልክት ስርቆት ተፈጽሞብኛል ሲል ኒው ዮርክ ለሚገኘው ፍርድ ቤት ኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) ጫማዎቹን ከመሸጥ እንዲታገድ እንዲሁም ዝነኛውን ምልክታቸውን እንዳይጠቀም እንዲከለከል ሲል ክስ መስርቶ ነበር።
"የሚስቺፍ ፈቃድ ያላገኘው የሰይጣን ጫማ ናይኪ እና ይህ የድርጅቱ ጫማ መካከል ግንኙነት ያለ በማስመሰል በደንበኞቻችን ላይ ግርታን እና ብዥታን ይፈጥራል" ሲል በክሱ ላይ ናይኪ አመልክቶ ነበር።
የሚስቺፍ ጠበቆች በበኩላቸው 666ቱ ጫማዎች "ስኒከሩን እንዲመስሉ ተደርገው የተሰሩ አይደሉም፤ ከዚያ ይልቅ በተናጠል እያንዳንዳቸው የጥበብ አሻራ ያረፈባቸው ምርቶች እና ለሰብሳቢዎች አንዱ በ1,018 ዶላር የሚሸጡ ናቸው" ሲሉ ተከራክረዋል።
ክሱን የተመለከቱት የፌደራሉ ዳኛ ለናይኪ በመወሰን ጊዜያዊ የእግድ ውሳኔ አስተላልፈዋል።
የዚህ ውሳኔ ተጽዕኖ ሚስቺፍ ላይ ምን እንደሆነ ባይገለፅም ተጨማሪ ጫማዎች ግን ለማምረት ፍላጎት እንደሌለው አስታውቋል።
ሚስቺፍ ባለጥቁርና ቀይ ቀለሙን ጫማ ለገበያ ያቀረበው ሰኞ ዕለት ሲሆን ይህም ተባባሪው ራፐር ሊል ናስ ኤክስ አርብ ዕለት በዩቲዩብ ከለቀቀው ሞንቴሮ (ኮል ሚ ባይ ዩር ኔም) የተሰኘ አዲስ ሙዚቃ ጋር ገጥሟል።
በሙዚቃ ቪዲዮው ላይ ራፐሩ ከመንግሥተ ሰማያት ወደ ሲኦል ተንሸራትቶ በመውረድ ከሰይጣን ጋር ሲደንስ እና ከዚያም ሰይጣኑን ገድሎ ዘውዱን ሲነጥቅ ይታያል።
በሙዚቃ ቪዲዮ ላይ የቀረበው ምሰላ እና ጫማው ላይ የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ከቁጥር 18 "ሰይጣንን ከሰማይ እንደመብረቅ ሲወድቅ አየሁ" የሚለውን ጥቅስ ለማመልከት ነው።
እያንዳንዱ ጫማ የናይኪን ሶል የያዘ ሲሆን 60 ኪዮቢክ ሴንቲሜትር ቀይ ቀለም እና ከጥበብ ሥራዎችን ከሚሰበስበው ድርጅት አባላት የተወሰደ ጠብታ የሰው ደም አለበት።
የስፖርት ጫማ አምራቹ ናይኪ ኒው ዮርክ ለሚገኝ ፍርድ ቤት ባስገባው ክስ ላይ ይህንን ተመሳስሎ የተሰራ 'የሰይጣን ጫማ' እንዲመረት አልፈቀድኩም ብሏል።
የቴናሲ ነዋሪ የሆነው ጆሴፍ ራሽ ጫማውን ለመግዛት 1,080 ዶላር መክፈሉን ገልጾ ገንዘቡ ቀልጦ እንዳይቀር ያለውን ስጋት ተናግሯል።
"እስከ ከፈልኩ ድረስ ጫማው ይደርሰኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ራሽ ጫማውን የገዛው ለማድረግ ሳይሆን ዝንባሌውን ለመግለጽ እና ለሃሳቡ ድጋፉን ለማሳየት መሆኑንም ገልጿል።
ሌላኛው ጫማውን የገዛው ማኬንዚ ኖሪስ በበኩሉ የሚስቺፍ የጥበብ ስብስቦች የረዥም ጊዜ ተከታታይ መሆኑን ገልጾ የናይኪ ክስ ጫማውን ገዝቶ አትርፎ ለመሸጥ የነበረውን እቅድ ማዛባቱን ይናገራል።
በናይኪ ክስ የተበሳጨው ኖሪስ ጫማውን መልሶ በ2500 ዶላር ለመሸጥ እቅድ እንደነበርው ተናግሯል።