የእንግሊዝ ፖሊሶች የዕፅ አዘዋዋሪዎችን ስልክ ቁጥሮች በመጠቀም ሱሰኞችን እየረዱ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Essex Police
በደቡብ ምስራቅ እንግሊዝ የምትገኘው የኢሴክስ ግዛት ፖሊሶች የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን ስልክ ቁጥሮች በመጠቀም ሱሰኛ የሆኑ ሰዎችን መለየት ጀምረዋል ተብሏል።
ፖሊሶቹ በግዛቲቷ ታዋቂ የሚባሉ አዘዋዋሪዎች ላይ ያገኙዋቸው ስልኮች ላይ መልዕክት ይልካሉ።
መልዕክቱም የአደንዛዥ ዕፅ ሱሶዎትን ማላቀቅ ከፈለጉ ዕርዳታ የሚሰጥ ድርጅት አለ፤ በዚህ ስልክ ማግኘት ይችላሉ በማለት ከስልክ ቁጥሩ ጋር አያይዘው ይልካሉ።
የግዛቲቷ ኢንስፔክተር ሊውስ ባስፎርድ እንዳሉት በዚህ መንገድም በሺዎች የሚቆጠሩ ሱሰኞችን ማግኘትና እርዳታ መለገስ እንደሚቻልም ያምናሉ።
"የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ወሮበሎች በዋነኝነት ኢላማ የሚያደርጉዋቸው ሱሰኞችንና በተለያየ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን ነው። ብዙዎች ከገቡበት አጣብቂኝ መውጣት አቅቷቸው ወይም እንዴት እርዳታ እንደሚያገኙ ፈርተው የሚኖሩ ናቸው" ብለዋል ኢንስፔክተሩ።
"ለነዚህ ሰዎች ማሳወቅ የምንፈልገው ከዚህ መውጣት ይቻላል። የሚረዷቸውም ሰዎች አሉ" ብለዋል።
"እነዚህን መልዕክቶች ለመላክ የምናወጣው ወጪ ትንሽ ነው። የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነትና የሚፈጥረው ጥገኝነት ዋጋ ግን ብዙ ያስከፍለናል" ብለዋል።
ከፖሊስ ጋር በመጣመር ይህንን ስራ እየሰራ ያለው ኦፕን ሮድ የተባለ እርዳታ ድርጅት ተወካይ ጆኒ ቶምሰን በበኩላቸው "የመጀመሪያዋን እርምጃ መራመድና እርዳታ እፈልጋለሁ ማለት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እናውቃለን" ይላሉ።
የእርዳታ ድርጅታቸው በባለፈው አመት 12 ሺህ ሱሰኞችን መርዳት እንደቻለም አስታውቀዋል። "በህይወታቸው አዎንታዊ ለውጥ እንዲያመጡና ያም ዘላቂ እንዲሆን እየሰራን ነው" ብለዋል
"ከ20 አመታት በላይ በሱስ ኖረው ከዚያ የተላቀቁ ሰዎችን እናውቃለን። መቼም ቢሆን ማገገም ይቻላል" በማለት ይናገራሉ።












