የአንድ ቢትኮይን ዋጋ 2.4 ሚሊዮን ብር ገባ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ60 ሺህ ዶላር ወይም 2.4 ሚሊዮን ብር በላይ በመግባት ክብረ ወሰን ሰብሯል።
ቢትኮይን መመንደግ የጀመረው በተለይ ደግሞ ከባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መገባደጃ አንስቶ ነው።
ይህንን የማይጨበጥ የማይዳሰስ መገበያያ ገንዘብ በርካታ ግዙፍ ድርጅቶች እንቀበለዋለን ማለታቸው ለዋጋው መናር ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
በዘርፉ ጥርስ የነቀሉ ግን የቦትኮይን ዋጋ እንዲህ ያሻቀበው የአሜሪካ መንግሥት በኮሮናቫይረስ ኪሳቸው ለተጎዳ ዜጎች የሰጠውን ድጎማ ተከትሎ ነው ይላሉ።
የቢትኮይን ጠቅላላ የገበያ ዋጋ አሁን ከ1 ትሪሊየን በላይ ሆኗል።
ቢሆንም ቢትኮይን ከተፈጠረበት የፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ ዋጋው አንድ ጊዜ ሲያሻቅብ አንዴ ደግሞ ሲያሽቆለቁል ነው የከረመው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የቢትኮይን ማሻቀብ ከግዙፍ ኩባንያዎች ጋር ይያያዛል።
ባለፈው ወር በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪናዎች የሚያመርተው ተስላ የተሰኘው ድርጅት ባለቤት የሆነው ኢላን መስክ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን መግዛቱን ይፋ አድርጎ ነበር።
አልፎም ድርጅቱ ተስላ ወደፊት ልክ እንደ ወረቀት ገንዘብ ለመገበያያነት እንደሚያውለው አስታውቆ ነበር።
ቢትኮይን ምንድነው?
ቢትኮይን ማለት በቀላል ቋንቋ፤ ዲጂታል ገንዘብ ወይም መገበያያ ነው ማለት ይቻላል።
ይህ መገበያያ በኪሳችን ተሸክመን እንደምንዞረው የብር ኖት ወይም ሳንቲም ሳይሆን 'ኦንላይን' የሚቀመጥ ዲጂታል ገንዘብ ነው።
ሌላው የቢትኮይንና የተቀሩት የክሪይፕቶከረንሲዎች ልዩ ባህሪ በመንግሥታት እና በባንኮች አለመታተማቸው እንዲሁም ቁጥጥር አለመደረጉ ነው።
ቢትኮይን የሚፈጠረው 'ማይኒንግ' በሚባል ሂደት ነው። በመላው ዓለም በኔትወርክ በተሳሰሩ ኮምፒውተሮች ቁጥጥር ይደረግበታል።
ለሚያቀርቡት ምርት እና አገልግሎት ቢትኮይንን በክፍያ መልክ የሚቀበሉ በርካቶች ድርጅቶች አሉ።
ማይክሮሶፍት፣ የፈጣን ምግብ አቅራቢዎቹ ኬኤፍሲ እና ሰብዌይ፣ የጉዞ ወኪሉ ኤክስፔዲያን ከመሳሰሉ ባለብዙ ሚሊዮን ገንዘብ ኩባንያዎችን አንስቶ እስከ ሆቴሎች እና ካፊቴሪያዎች ቢትኮይንን በክፍያ መልክ ይቀበላሉ።
ቢትኮይንን በመጠቀም የገዢው ማንነት ይፋ ሳይደረግ በየትኛውም ሰዓት እና በየትኛውም ስፍራ የቢትኮይን ዝውውር ማድረግ ይቻላል።
ሕገ-ወጥ ቡድኖች የጦር መሳሪያዎች እና እጾችን ሊገዙ እና ሊሽጡ ይቻላሉ፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና አሸባሪዎችን ለመደገፍ ያስችላል በማለት ቢትኮይንን ጨምሮ ሌሎች ክሪይፕቶከረንሲዎች ላይ ያላቸውን ስጋት የሚያነሱ በርካቶች ናቸው።












