ቅዳሜ ዕለት በሆሮ ጉድሩ በታጣቂዎች ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

ካርታ
የምስሉ መግለጫ, አቤ ዶንጎሮ ወረዳ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ ይገኛል

በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጉር ወረዳ ዳቢስ በሚባል ቀበሌ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 22 ሰዎች መገደላቸውን የዞኑ አስተዳዳሪና የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለፁ።

ቢቢሲ ካናገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዱ እንደገለጹት ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 27/2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት ግለሰቦች የቀብር ሥነ ሥርዓት ሰኞ ዕለት ተፈጽሟል።

ግለሰቡ አክለውም ጥቃቱ ያነጣጠረው "በአካባቢው በሚኖሩ የአማራ ብሔር አባላት ላይ መሆኑን" የገልጹ ሲሆን፤ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ደቻሳ ይህንኑ አረጋግጠዋል።

አቶ በቀለ ስለተፈጸመው ግድያ ሲያብራሩ "የካቲት 27 በዞናችን ውስጥ በምትገኘው አቤ ደንጎሮ ወረዳ ዳቢስ በምትባል በደን ወደተከበበች ቀበሌ ታጣቂዎቹ በመምጣት ከነዋሪዎቹ ሞባይላቸውን ሰብስበው ጥቃት ፈጽመውባቸዋል" ብለዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት 22 ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን ገልፀዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆኑ አስተዳዳሪው ጥቃቱ የተፈጸመው ነዋሪዎች ባላሰቡበት እና መደበኛ ሕይወታቸውን እየመሩ ባሉበት ወቅት መሆኑን ገልፀው፣ "ጥቃቱን የፈጸሙት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው" ብለዋል።

የሆሮ ጉዱሮ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ በቀለ ደቻሳ፣ በአካባቢው ሸኔ የሚባል ኃይል አባ ቶርቤ ከሚባል ቡድን ጋር ተቀናጅቶ በሰላማዊ ዜጎች፣ በመንግሥት ባለስልጣናት እና በፀጥታ አካላት ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደነበር አስታውሰዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 27/2013 ዓ.ም የተፈፀመው የዚሁ ድርጊት አካል መሆኑንም ይናገራሉ።

ታጣቂዎቹ የአካባቢ ሰዎች በሥራቸው ላይ እያሉ አቅም የሌላቸውን ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶችን ለይተው ጥቃት ማድረሳቸውን አስተዳዳሪው ጨምረው ገልፀዋል።

በወቅቱ ቢያንስ 17 ሰዎች በተለያዩ የጦር መሳሪያዎች መገደላቸውን የገለጹት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከሟቾቹ በተጨማሪ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 28 ሰዎች ታግተው ወደ ጫካ መወሰዳቸውንም ገልጸዋል።

አቶ በቀለ በታጣቂዎቹ ታግተዋል ስለተባሉት ሰዎች ሲናገሩ "በወቅቱ ታፍነው የተወሰዱ ቢኖሩም ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ ተለቅቀው ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል" ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱ መፈጸሙን ተከትሎ የክልሉ ልዩ ኃይል ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በቦታው መድረሱን ተናግረው፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ያሏቸው ቡድኖች ከርቀት በልዩ ኃይሉ ላይ ጥቃት በመፈፀማቸው "ወደ እኛ ሳይደርሱ ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ ተመልሷል" ብለዋል።

የጸጥታው ሁኔታ ከቅዳሜ ጀምሮ አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያትም፣ የተገደሉት ሰዎች እስከ እሁድ ድረስ አስከሬናቸው ከተገደሉበት ቦታ ሳይነሳ መቆየቱን ተናግረዋል።

አቶ በቀለ ደቻሳ በበኩላቸው ጥቃቱ የተፈፀመው በአካባቢው ተሰማርቶ የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ለሥራ ተጠርቶ ወደ ሌላ አካባቢ መሄዱን ተከትሎ መሆኑን ገልጸው፣ ጥቃት መድረሱ እንደተሰማ ወደ ስፍራው ቢመለስም መንገድ ላይ ያደፈጠ ኃይል ጥቃት እንደፈፀመበት ተናግረዋል።

ተጨማሪ ኃይል ከሌላ አካባቢ እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ ግን፣ የአካባቢውን ሰላም ማስከበር መቻሉን የሟቾች አስከሬንም እንዲነሳ ተደርጎ ሰኞ ዕለት ቀብራቸው ተፈጽሟል ብለዋል።

ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ ጥቃቱ በወረዳው አራት ቀበሌዎች ውስጥ መፈጸሙን ይናገራሉ።

በዚህም ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በአንድ ኤፍኤስአር እና ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች ተጭነው በመምጣት ቀጥታ በነዋሪው ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ይገልጻሉ።

በቀበሌዋ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች መገደላቸውን የሚናገሩት ነዋሪ፣ አንድ ቤተክርስቲያን መቃጠሉንም ይናገረሉ። ቢቢሲ ይህንን ከአካባቢው አስተዳዳሪ ማረጋገጥ አልቻለም።

ከጥቃቱ በኋላ በቦታው የፌደራል ፖሊስ ቢደርስም፣ ነገር ግን ተመሳሳይ ግጭት ወደ ተከሰተበት ሌላ ቦታ በመሄዱ አሁንም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ።

አብዛኛው ሰውም ከሚከፈትበት ጥቃት ለማምለጥ ሲባል ሕጻናት እና አዛውንቶች ሳይቀሩ ወደጫካ ገብተው መደበቃቸውን ገልጸዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪ በአሁኑ ጊዜ አካባቢው ወደ ቀደመ ሰላሙ መመለሱን ለቢቢሲ ተናግረው፣ "ከቀያቸው ለጊዜው በስጋት ሸሽተው የነበሩ አሁን ተመልሰው በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ" ብለዋል።

'የኦነግ ሸኔ' ታጣቂዎች በብዛት ይንቀሳቀሱባቸዋል በሚባሉት የወለጋ ዞኖችም በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ጥቃቶች በንጹሃን ዜጎች ላይ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ እንደነበር ይታወሳል።

የክልሉ መንግሥትና የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ታጣቂው ቡድንን ለመቆጣጠር በተለያዩ ጊዜያት እርምጃዎችን መውሰዳቸውንና በዚህም ከቡድኑ አባላት መካከል የተገደሉና የተያዙ እንዳሉ ተነግሯል።

ቢሆንም ግን ታጣቂ ቡድኑ ይንቀሳቀስባቸዋል በሚባልባቸው የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በነዋሪዎች፣ በአካባቢ ባለስልጣናትና በጸጥታ አካላት ላይ የሚፈጽመው ጥቃት አልተቋረጠም።