ትግራይ- የአክሱም 'ቄስ' የተባለው ግለሰብና የፈጠረው ውዝግብ

የፎቶው ባለመብት, Twitter
ባለፈው ሳምንት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባካሄደው ምርመራ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የኤርትራና ወታደሮች በአክሱም ከተማ ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ይፋ ካደረገ በኋላ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ነዋሪነቱን በአሜሪካ ያደረገ ግለሰብ "በሀሰት ራሱን የአክሱም ጽዮን ማርያም ካህን ነኝ" በማለት ስለ ክስተቱ መረጃ ሰጥቷል ሲሉ ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም የአምነስቲን የምርመራ ሪፖርት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ "እንደ መረጃ ምንጭ ሆኖ የተጠቀሰው [በአምንስቲ ሪፖርት ላይ] አንድ ግለሰብ እንደሚለው የአክሱም ቄስ ሳይሆን ቦስተን የሚኖር ግለሰብ ሆኖ ተገኝቷል" ብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በዚያው ዕለት ቄሱን " አታላዩ" ሲል ዘግቧል።
ይኸው የመገናኛ ብዙኀን መቀመጫቸውን ኒውዮርክ ያደረጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አባ ጴጥሮስ የተባሉ ካህንን ጠቅሶ፣ በቪዲዮው ላይ የሚታየው ግለሰብ የቤተክርስትያኒቱ ተከታይ አለመሆኑን ዘግቧል።
ይህ ዘገባ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በሆኑት ፍፁም አረጋ ይፋዊ የትዊተር ሰሌዳ ላይ ተጋርቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም በበኩሉ ለቢቢሲ የዚህ ግለሰብ ቪዲዮ ላይ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌለው አረጋግጧል።
ታዲያ በትክክል የሆነው ምንድን ነው? ራሱን ቄስ ነኝ በማለት በሀሰት ያቀረበስ አለ?
አክሱም ላይ የተሰራው ዘጋቢ ፊልም
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የአምነስቲ ሪፖርት በወጣበት አርብ ዕለት በዩቲዩብ ላይ ከተለቀቀው ዘጋቢ ፊልሙ ላይ የተወሰዱ ቅንጭብጭብ ቪዲዮዎችን ሲያጋሩ ነበር።
የተወሰኑት ቪዲዮዎች ነዋሪነቱ አሜሪካ ቦስተን የሆነውን የሚካዔል በርሄን ምስል በመጨመር "በሀሰት ቄስ' ስለማለቱ ጽሁፍ ጨምረው አጋርተውታል።
ይህንን ቪዲዮ ያዘጋጁት ሰዎች ግለሰቡ በአክሱም የደረሰውን ተጎጅ ታሪክ በድምፅ የተረከው ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
አክለውም ግለሰቡ "የተጎጂዎች ድምጽ" እንዲሆን መፈለጋቸውንና፣ ይህንንም በግልጽ ማስቀመጣቸውን ይናገራሉ።
ሳይቆራረጥ በዩቲዮብ ላይ የተለቀቀው ቪዲዮ በመግቢያው ላይ "የተጎጂዎቹ ታሪክ በሌሎች ግለሰቦች ተተውኗል" (re-enactment) የሚል መግለጫ ተካትቶበታል።
ይህም ማለት በቪዲዮው ላይ የሚታየው ምስል እና የሚሰማው ድምጽ በትክክል የተጎጂዎቹ አይደለም ማለት ነው።
ይህንን ዘጋቢ ፊልም የሚያስተዋውቀው አንድ ፖስተር ላይም ይኸው ማሳሰቢያ በግልጽ ሰፍሮበት ይታያል።
ይኹን እንጂ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከሁለት ቀናት በፊት ዘጋቢ ፊልሙን ለማስተዋወቅ የተሰራጨው አጭር ቪዲዮ ላይ ግን ይህ ማሳሰቢያ አልተካተተበትም።
የተወሰኑ ምስሎች ከታዩ በኋላ በቀጥታ ወደዚህ የአንድ ካህንን ታሪክ ወደ ተወነው ግለሰብ ያልፋል።
"ቄስ ወልደማርያም እባላለሁ፤ በሕዳር ወር በአክሱም ጽዮን ማርያም ፀሎት ላይ ነበርን " ሲል ይታያል ግለሰቡ።
" ልናስቆማቸው ግን አልቻልንም፤ ሁላችንም ላይ መተኮስ ጀመሩ" ይላል ሌላ ስፍራ ደግሞ።
ከዚህ ቪዲዮ ጀርባ ያለው ማን ነው?
ቪዲዮው በዩቲዩብ ላይ የተለቀቀው በትግራይ ሚዲያ ሀውስ አማኻኝነት ነው። ትግራይ ሚዲያ ሀውስ በትግራይ ጉዳይ ላይ አተኩሮ የሚሰራ የኦንላየን ሚዲያ ሲሆን፣ ራሱን ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት በማለት ይገልጻል።
ይህ ቪዲዮ ግን ፕሮዲውስ የተደረገው በ መርሃዊ ዌልስ ቦግ እና ስታንድ ዊዝ ትግራይ የተሰኘው ቡድን መስራች በሆኑት ሉዋም ግደይ እና ራህዋ ግደይ ጋር በጥምረት ነው።
በዚህ ቪዲዮ ላይ መርሃዊ እና ልዋም ዳይሬክተሮች መሆናቸውም ተጠቅሷል።
በዘጋቢ ፊልሙ ላይ እንደ ቄስ በመሆን የተወነው እና በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን መነጋገሪያ የሆነው ሚካኤል በርሄም በዘጋቢ ፊልሙ ላይ የተሳተፉ ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ታከትቶ ይታያል።
መርሃዊ በኦንላየን ላይ በስፋት የሚንቀሳቀስ ግለሰብ ነው። ከተለያዩ እንግዶች ጋር በመሆንም በየሳምንቱ በቀጥታ በትግራይ ስላለው ግጭት ይወያያል። በታህሳስ ወርም በርሄ ቋሚ እንግዳ በመሆንም ይቀርብ ነበር።
መርሃዊ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ዘጋቢ ፊልሙ የተዘጋጀው ቦስተን በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች መሆኑን ጽፏል።
ራሱንም ሲገልጽ የማህበረሰብ አደራጅ (community organizer)ብሎ ነው።
" ይህንን ነገር ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ሚካዔል በርሄ ቄስ አይደለም፤ እንደ ቄስ በመሆን የተወነ ነው" ሲል ስለ ሁኔታው ለቢቢሲ አብራርቷል።
"ሆሊውድ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ሁሌ ይሰራል። ሆሊውድ ስለ ኢየሱስ ክርስተስ ቪዲዮዎችን በመስራት መጠመዱን አታውቁምን? ኢየሱስ ክርስቶስን በመሆን ይተውናሉ ነገር ግን አይደሉም፣ ትወና ነው።"
ልዋም እንዳለችው ይህንን ቪዲዮ ያዘጋጁት ታሪካቸውን ለመናገር መንገድ ለሌላቸው ተጎጂዎች ድምጽ ለመሆን በማሰብ ነው።
ቢሆንም ግን በመንግሥት እና በተቺዎች ግብረ መልስ መገረሟን አልሸሸገችም።
ከመንግሥት ወገን ይህንን አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች የተመለከቱት ዘጋቢ ፊልሙን ለማስተዋወቅ የተሰራውን አጭር ቪዲዮ ብቻ እንደሚሆን እንደምታምን አክላ ገልጻለች።
በተጨማሪም "ማስታወቂያውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ስናጋራ አርብ ለእይታ እንደሚበቃ ገልፀን ነበር፣ ስለዚህ በርካታ ሰዎች፣ የሚጠሉንን ሰዎች ጨምሮ፣ ምናልባት ሙሉ ቪዲዮው ያ ብቻ መስሏቸው ሊሆን ይችላል" ብላለች።
" የማይክን (ሚካኤል በርሄን) ስክሪንሾት በማምጣት ልክ ቦስተን እንደሚኖር ፣ ቄስ አለመሆኑን እንደደረሱበት አስመስለው አቀረቡ። በጣም አስቂኝ አስተያየቶች አሉ ልክ በጥይት ተመትቶ በሕይወት እንደተረፈ እና እንደሚናገር ያለ።"
ራህዋ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከተጠቃሚዎች፣ እነርሱን በማካተት በርካታ አስተያየቶች እንደደረሳቸው ትገልፃለች።
"ካነበብኳቸውና ካሳቁኝ መካከል ቄሱ ቆዳውን ለመንከባከብ የሚቀባው ምን እንደሆነ ትነግሩናላችሁ፤ የሚለው ነው ይህ በጣም ነው ያሳቀኝ" ትላለች።
ከአምንስቲኢንተርናሽናል ጋር ግንኙነት ነበረው?
መርሃዊ የእነርሱ ዘጋቢ ፊልም የአምንስቲ ሪፖርት ከወጣበት ቀን ጋር መገጣጠሙ "ያጋጣሚ ጉዳይ ነው" ይላል።
" ወቅቱ በመግጠሙ ሰምሯል። ስለአክሱም ጭፍጨፋ ሪፖርት እንደሚወጣ አናውቅም ነበር ፤ እና ቪዲዮውን ለቅቀን ግንዛቤ እንፍጠር የሚለው ሃሳብ ብቻ ነው የነበረን" ሲል አክሏል።
የአምነስቲ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ከዘጋቢ ፊልሙ ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
ኮኖር ፎርቹን ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ "አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደ ቄስ በመሆን ከተወነው ግለሰብ ጋር ወይንም ደግሞ ቪዲዮውን ከሰሩት ግለሰቦች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። በምንም ዓይነት ቪዲዮውን የተጠቀምንበት ወይንም ያጣቀስንበትም አጋጣሚ የለም" ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
"የማህበራዊ ሚዲያ ሴራ ተንታኞች ከእኛ ጋር አገናኝተው እስኪናገሩ ድረስ እና በሚገርም ሁኔታ የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርም ያንኑ ተቀብሎ እስኪያስተጋባ ድረስ ስለመኖሩም ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም"
ራህዋ ግደይ እነርሱ በዘጋቢ ፊልሞቻቸው ውስጥ ታሪካቸውን የተጠቀሙት ሰዎች ለአምንስቲም ምስክርነታቸውን ሰጥተው ሊሆን እንደሚችል ታምናለች። ነገር ግን ይህ በስራቸው ውስጥ ጥልቅ ጥናት ማካሄዳቸውን እንደሚያሳይ ገልጻለች።
"በእኛ ቪዲዮ ውስጥ ካለ ባለታሪክ ጋር ተመሳሳይ ታሪክ ያለው አይቻለሁ፤ ያ ማለት እኛ ጥናታችንን አካሂደናል። ቀድመን ነበር እንዲሁም በትግራይ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ እያንዳንዱን ነገር እየተከታተልን ነው" ስትል ታክላለች።
" አሜሪካ ስለምንኖር ምስክር መሆን አንችልም ነገር ግን ጥናት እንሰራለን፤ በስፍራው ካለ ሕዝባችን ጋር እጅና ጓንት ሆነን እንሰራለን" ትላለች
ልዋም ግደይ የእነርሱን ቪዲዮ ላይ ዘመቻ የተከፈተበት ምክንያት ትኩረትን ለማስቀየር እንደሆነ እንደምታምን ገልጻ ነገር ግን የበለጠ ግፊት ሰጥቶናል ብላለች።
"አሁን ወደፊት መገስገስ መቀጠል አለብን" ስትልም ሃሳቧን ትቋጫለች።















