ኮሮናቫይረስ ፡ አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠው የኮቪድ-19 ክትባት አሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ተፈቀደ

የዩናይትድ ስቴትስ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣናት አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠውን ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተሰኘው የኮቪድ-19 ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ሰጡ።

ክትባቱ ፋይዘርና ሞደርና ከተሰኙት ሌሎች ክትባቶች ጋር ሲነፃፀር ዋጋው አነስተኛ ነው ተብሏል። አልፎም እንደ ሌሎቹ ክትባቶች ፍሪጅ ውስጥ እንጂ ፍሪዘር [በረዶ የሚሰራ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ያለበት] ውስጥ ማስቀመጥ አያስፈልገውም ተብሏል።

ሙከራዎች እንደሚያመለክቱት ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ሰዎች በጣም እንዳይታመሙ ይረዳል፤ ነገር ግን አነስተኛ ሕመም ባላቸው ላይ ያለው ውጤታማነት 66 በመቶ ነው።

ክትባቱ በቤልጂየሙ ኩባንያ ያንሰን የተመረተ ነው።

ኩባንያ በሚቀጥለው ሰኔ ወር መጨረሻ 100 ሚሊዮን ብልቃጦች አምርቶ ለአሜሪካ ለመስጠት ቃል ገብቷል።

ቢሆንም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ክትባቱ አሜሪካ ውስጥ መታደል እንደሚጀምር ታውቋል።

ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውሮፓ ሕብረት እንዲሁም ካናዳ ከክትባቱ እንዲደርሳቸው ያዘዙ ሲሆን 500 ሚሊዮን ብልቃጦች ደግሞ ኮቫክስ በተሰኘው ፕሮግራም መሠረት የመግዛት አቅም ለሌላቸው ሃገራት ይከፋፈላሉ።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን "ይህ ለአሜሪካዊያን አስደሳች ዜና ነው፤ ዕድገትም የታየበት ነው" ብለዋል።

"ምንም እንኳ የዛሬውን ዜና በደስታ ብንቀበለውም ሁሉም አሜሪካዊያን እጃቸውን እንዲታጠቡ፣ ርቀታቸውን እንዲጠብቁና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ እንዲቀጥሉ ማሳሳብ እወዳለሁ" ብለዋል በመግለጫቸው።

ገለልተኛ የሆኑ ሙያተኞች ክትባቱን ካፀደቁት በኋላ ነው የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ለክትባቱ ፈቃድ የሰጠው።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ደቡብ አፍሪካና ብራዚል ውስጥ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ክትባቱ ጠንከር ያለ ሕመምን በመከላከል ረገድ 85 በመቶ ውጤታማ ነው።

መካከለኛ ደረጃ የሚባለውን ሕመም በመከላከል ደግሞ 66 በመቶ ውጤታማነትን አሳይቷል።

ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ሰዎች ለ28 ቀናት ክትትል የተረገባቸው ሲሆን አንድም ሰው አልሞተም በጎንዮሽ ጉዳት ምክንያት ወደ ሆስፒታል አልተወሰደም።

ነገር ግን አዳዲስ የኮቪድ-19 ዝርያዎች የታዩባቸው ብራዚልና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የክትባቱ መከላከል አቅም ዝቅ ያለ ቢሆንም ከባድ ሕመምን በመከላከል ግን እመርታ አሳይቷል።

ደቡብ አፍሪካ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት በጥናት መልክ የጤና ሙያተኞች እንዲወስዱት ማድረግ ጀምራ ነበር።

ኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ የተሰኘው ክትባት በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ላይ ያለው ውጤታማነት ዝቅተኛ ነው መባሉን ተከትሎ ነው ደቡብ አፍሪካ ወደ አዲሱ ክትባት ያመራችው።

ክትባቱ አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሁም በአነስተኛ የጤና ሙያተኞች መስጠት ይቻላል።

ዩናይትድ ኪንግደም 30 ሚሊዮን ክትባት እንዲደርሳት ትዕዛዝ ሰጥታለች፤ የአውሮፓ ሕብረት ደግሞ 200 ሚሊዮን።

ካናዳ ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን 38 ሚሊዮን ክትባት እንደሚደርሳት ተሰምቷል፤ ኮቫክስ የተሰኘው ፕሮግራም ደግሞ ግማሽ ቢሊዮን ብልቃጥ ክትባት ይደርሰዋል።

አሜሪካ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከ78 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ክትባት አግኝተዋል። ይህ በቀን ሲሰላ አንድ 1.3 ሚሊዮን ማለት ነው።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት 100 ሚሊዮን ሰዎች ለማስከተብ ቃል ገብተዋል።

አሜሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አጥታለች።

ነገር ግን አዳዲስ የሚያዙ ሰዎች፣ ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥርና ሞት እየቀነሰ ነው።

የጤና ባለሙያዎች ግን ጥንቃቄ ከሌለ ቫይረሱ እንደ አዲስ ሊያገረሽ ይችላል ይላሉ።