ኮሮናቫይረስ ፡ ለኢትዮጵያና ለሌሎች አገራት ይሆናል የተባለው የኮቪድ-19 ክትባት መሠራጨት ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, UNICEF GHANA
ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሌሎች አገራት የኮቪድ-19 ክትባትን ያቀርባል የተባለው የኮቫክስ የክትባት አቅርቦት ፕሮግራም በአፍሪካ ውስጥ መሰራጨት ጀመረ።
በዚህም መሠረት የመጀመሪያው የኮቫክስ ክትባት ጋና በመቀበል የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
በዓለም ጤና ድርጅት መሪነት የተዘረጋው ይህ ሥርዓት የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ለሁሉም የዓለም አገራት በፍትሃዊ መንገድ እንዲከፋፈሉ ለማድረግ ያለመ ነው።
ኮቫክስ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ሁለት ቢሊየን የኮቪድ-19 ክትባቶችን በዓለም ዙሪያ የማሠራጨት ዕቅድ አለው።
በአስትራዜኔካና በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተመረቱ 600 ሺህ ብልቃጥ ክትባቶች ዛሬ ረቡዕ የጋና ዋና ከተማ አክራ ደርሰዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግሥት የሕፃናት መርጃ [ዩኒሴፍ] ባወጡት መግለጫ "እጅግ ጠቃሚ እርምጃ ነው" ብለዋል።
"የኮቪድ-19 ክትባቶች ጋና መድረሳቸው ወረርሽኙን ለማጥፋት አንድ እርምጃ ወደፊት መራመድ ነው" ብለዋል ድርጅቶቹ።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙባት 580 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ነገር ግን ጋና የምትመረምረው ሰው ብዛት አናሳ በመሆኑ ነው እንጂ ቁጥሩ ከዚህ በላይ ነው ተብሎ ይታመናል።
ኮቫክስ ምንድነው?
የኮሮናቫይረስ ክትባት ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ ወዲህ ሃብታም የሚባሉቱ አገራት ናቸው ክትባቱን በገፍ እየገዙ ዜጎቻቸውን እየከተቡ ያሉት።
በዶክተር ቴድሮስ መሥሪያ ቤት አማካይነት የተዘረጋው ኮቫክስ የተሰኘው ማዕቀፍ ደሃ አገራት ክትባቱን ለማግኘት ብዙ እንዳይጠብቁ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል።
በዚህ ማዕቀፍ መሠረት ሃብታሞቹ አገራት አቅም የሌላቸውን አገራት በገንዘብ እንዲያግዙ ይደረጋሉ።
በአንድ ዓመት ብቻ በ190 አገራት ሁለት ቢሊዮን ክትባቶችን ለማሠራጨት ታልሟል።
በተለይ ደግሞ 92 ደሃ የሚባሉ አገራት ከሌሎች 98 አቅም ካላቸው አገራት እኩል ክትባቱን እንዲቀበሉ ይደረጋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ናቸው።
ነገር ግን እንደ ሴኔጋል ያሉ ጥቂት አገራት ከዚህ ማዕቀፍ ውጭ ክትባት ማግኘት ችለዋል።
ፕሮግራሙ እስካሁን ድረስ ለክትባት የሚሆን 6 በሊየን ዶላር ማሳበሳብ ችሏል። ቢሆንም ተጨማሪ 2 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል እየተባለ ነው።
ምንም እንኳ ፕሮግራሙ ቀርፋፋ ነው እየተባለ ቢተችም የዓለም ጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ አሁን ጋና የደረሰው ክትባት የመጀመሪያው ዙር ነው ብለዋል።















