ትግራይ ፡ በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በመላው ትግራይ ዳግም ኃይል ተቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመላው የትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዳግም መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የኃይል መቋረጥ ያጋጠመው ማክሰኞ የካቲት 09/2013 ዓ. ም ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ነው።
በመላው አገሪቱ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚያስተዳድረው ተቋሙ እንዳለው "የጁንታው ርዝራዦች" ያላቸው በክልሉ ባለ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በፈፀሙት ጥቃት በመላው ትግራይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቋረጡን ገልጿል።
የተጠቀሱት ኃይሎች አዲጉዶም ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከአላማጣ - መሆኒ - መቀለ በተዘረጋ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በፈጸሙት ጥቃት በክልሉ ኤሌክትሪክ መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጿል።
የትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከሚያገኝባቸው መስመሮች አንዱ የሆነውና ጥቃት የተፈጸመበት የአላማጣ - መሆኒ - መለለ መስመር ሲሆን ሌላኛው የተከዜ አክሱም መስመር ደግሞ የጥገና ሥራው እየተከናወነ እንደነበር ድርጅቱ ገልጿል።
"የተቆረጠው ማስተላለፊያ መስመር ነው። ይህ ነው ኃይል እንዲቋረጥ ያደረገው። ጉዳቱ ይሄ ብቻ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልቃል። ሌሎች ጉዳቶች ደርሰው ከሆነ ግን መስመሮቹን መፈተሽ ያስፈልጋል" ብለዋል አቶ ሞገስ።
በደረሰበት ጥቃት ለኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ምክንያት የሆነው ይህ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረ ሲሆን ለመጠገንም ረዘም ያለ ጊዜ እንደወሰደ ተቋሙ አመልክቷል።
በጥቅምት ወር መጨራሻ ላይ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በደረሰ ጉዳት ለረዥም ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ የነበረ ሲሆን በክልሉ ያሉ የተለያዩ አካባቢዎች ኃይል መልሰው ለማግኘት ረዘም ላለ ጊዜ ለመጠበቅ ተገደው ቆይተው ነበር።
በትግራይ ክልል ውስጥ በተዘረጉ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ ሕዝቡ ከኃይል አቅርቦት ውጪ ከመሆኑ ባሻገር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የወጣባቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች መውደማቸው መገለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በደረሰባቸው ጥቃት ከአገልግሎት ውጪ የሆኑትን ለትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀርብባቸውን መሠረተ ልማቶች በመጠገን የክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲመለስ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትናንትናው ዕለት፣ ማክሰኞ፣ በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ላይ ባስተላለፈው መግለጫ ክልሉ እንዳይረጋጋ ለማድረግ የሚሞክሩ "የተበተኑ የህወሓት ኃይሎች" እንዳሉና ሕዝቡም ለእነዚህ ኃይሎች መጠጊያ እንዳይሰጥ ማሳሰቡ ይታወቃል።
ጊዜያዊው አስተዳደር በመግለጫው "የተበተኑ" ያላቸው የህወሓት ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ መሸሸጋቸውን አመልክቶ "የጥፋት ኃይሎች በመንደሮችና በከተሞች ውስጥ ተሰማርተው የሕዝቡን ሠላም በማናጋት ወደ ሌላ የከፋ ቀውስ እንዲገባ እየሠሩ ነው" ብሏል።
ጨምሮም በእነዚህ ኃይሎች ላይ ሊወሰድ በሚችለው እርምጃ ሕዝቡ እንዳይጎዳ "የጥፋት ኃይሎቹን አሳልፎ እንዲሰጥ ወይም ለደኅንነቱ ሲል ራሱን ከእነዚህ ኃይሎች እንዲያርቅ" አሳስቧል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የፌደራል መንግሥት በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ የክልሉ አስተዳዳሪ የነበረው የህወሓት አመራሮች ከስልጣን በማስወገድ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መደረጉ ይታወሳል።
ወታደራዊ ግጭቱን ተከትሎ በክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል በመቋረጡ ምክንያት የውሃ፣ የባንክ፣ የስልክ፣ የኢንተርኔትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ለረዥም ጊዜ ተቋርጠው ቆይተው አብዛኛው የክልሉ አካባቢ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘው በቅርቡ ነበር።
















