የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሕዝቡ የህወሓት ኃይሎችን እንዳያስጠጋ አሳሰበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉ እንዳይረጋጋ ለማድረግ የሚሞክሩ "የተበተኑ የህወሓት ኃይሎችን" መጠጊያ እንዳይሰጥ አሳሰበ።
ጊዜያዊው አስተዳደር ማክሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ "የተበተኑ" የህወሓት ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ ተሸሽገዋል በማለት አመልክቷል።
በመግለጫው "የጥፋት ኃይሎች በመንደሮችና በከተሞች ውስጥ ተሰማርተው የሕዝቡን ሠላም በማናጋት ወደ ሌላ የከፋ ቀውስ እንዲገባ እየሰሩ ነው" ብሏል።
በትናንትናው ዕለት፣ ማክሰኞ ፣ በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ላይ በቀረበው እና ከጊዜያዊው አስተዳደር የወጣው ይህ መግለጫ እንዳስጠነቀቀው፣ ሊወሰድ በሚችለው እርምጃ ሕዝቡ እንዳይጎዳ "የጥፋት ኃይሎቹን አሳልፎ እንዲሰጥ ወይም ለደኅንነቱ ሲል ራሱን ከእነዚህ ኃይሎች እንዲያርቅ" አሳስቧል።
በተጨማሪም የክልሉ ነዋሪ ከምሽት 12 ሰዓት አስከ ንጋት 12 ሰዓት የተደነገገውን ሰዓት እላፊ ጨምሮ ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውሳኔዎችን እንዲያከብሩም አሳስቧል።
መግለጫው ህወሓትን የተካው ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ጸጥታ ለማስፈን፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና የህዝቡን መብቶች ለማስከበር እየሰራ መሆኑን ገልጾ ሕዝቡ እንዲደግፈው ጥሪ አቅርቧል።
የትግራይ ክልልን ለ30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በብቸኝነት ያስተዳደረው ህወሓት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በተናጠል ምርጫ ማካሄዱን ተከትሎ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር አለመግባባት ውስጥ ከገባ በኋላ በሰሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ወታደራዊ ግጭት መከሰቱ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ መንግሥት ሕግ ማስከበር ባለው ወታደራዊ ዘመቻ በሦስት ሳምንት ውስጥ የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን በመቆጣጠር የህወሓት አመራሮችን ከስልጣን አስወግዷል።
የፌደራል ሠራዊት በህወሓት ኃይሎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ በከፈተበት ጊዜ የፌደሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል ምክር ቤትና አስተዳደር እንዲበተን በማዘዝ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ተደርጓል።
ከዚህ በኋላም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓት ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን ማረጋገጡን በመግለጽ ሰርዞታል።
በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች አሁንም አልፎ አልፎ ግጭቶች እንደሚያጋጥሙ የተነገረ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ ተቀስቅሶ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ለተለያዩ ሰብዓዊ ቀውሶች መጋለጣቸው ይታወቃል።
ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው ወደ ሱዳን ሲሰደዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ የለጋሽ ድርጅቶችን ድጋፍ ጠባቂ መሆናቸውን የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመግለጫዎቻቸው አመልክተዋል።















