ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ኩባ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማምረት የምታደርገው ጥረት ይሳካ ይሆን?
በኩባዋ ዋና ከተማ ሃቫና የሚገኘው ፊንሌይ የክትባት ኢንስቲትዩት ምናልባት ከሌሎች የዓለማችን ማዕከላት አንጻር ሲታይ ያረጀና ጊዜ ያለፈበት ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን በዚህ ማዕከል የሚሰራው የምርምር ሥራ እጅግ ዘመናዊ ነው።
የአገሪቱ ከፍተኛ ተመራማሪዎች እረፍት አልባ ረጅም ፈረቃዎችን ጭምር በመስራት ለኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ መፍትሄ ለማግኘት ደፋ ቀና እያሉ ነው። የክትባቱ ስም 'ሶቤሬና 2' የሚባል ሲሆን በኩባ ተመራማሪዎች ኩባ ውስጥ የተሰራ ነው።
ይህ ክትባት በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች ላይ ይሞከራል።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ባለፉት ሳምንታት በተደረጉ ክሊኒካዊ ሙከራዎች በጣም አመርቂ የሚባል ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ይህ አገሪቱ ክትባቱን ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢንስቲትይቱ ዳይሬክተር ዶክተር ቪሴንቴ ቬሬዝ ቤንኮሞ ገልጸዋል።
በኩባ መንግሥት እቅድ መሰረት ክትባቱ ክሊኒካዊ ሙከራውን ከጨረሰ በኋላ በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ለሁሉም ዜጎች መሰጠት ይጀመራል።
"የእኛ እቅድ በመጀመሪያ ሕዝባችንን መከተብ ነው'' ይላሉ ዶክተር ቪሴንቴ። "ከሕዝባችን በኋላ ምናልባት ለሌሎች አገራት መላክ ልንጀምር እንችላለን። ከ2021 መጨረሻ በኋላ ምናልባት 100 ሚሊየን የክትባት ብልቃጦችን አምርተን ሕዝባችን ሙሉ በሙሉ ለመከተብ እቅድ ይዘናል።"
ይህ ክትባት የአሜሪካም ሆነ የየትኛውም አገር እርዳታ አልተደረገለትም። ኩባ በባዮቴክኖሎጂ ከ30 ዓመታት በላይ ልምድ ያላት አገር እንደመሆኗ ይህ ምንም የሚገርም ነገር አይደለም።
በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ የኩባ ሳይንቲስቶች ለማጅራት ገትር ቢ (ሚኒንጃይተስ) ክትባት ካመረቱ የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ የወቅቱ የአገሪቱ መሪ ፊደል ካስትሮ መሰል ሥራዎችን ለማበረታታት ነበር ፊንሌይ የክትባት ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም ያደረጉት።
በአሜሪካ መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች የሚሰሩ መድኃኒቶች ወደ ኩባ እንዳይገቡ ሲደረግ አገሪቱ በራሷ መንገድ መድኃኒቶቹን ማምረት ትችላለች በማለት ፊደል ካስትሮ ይከራከሩ ነበር።
ነገር ግን አሁን ባለው ቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ አሰራር እንኳን ያለ ሌሎች አገራት ድጋፍና እርዳታ 100 ሚሊዮን የክትባት ብልቃጦችን አምርቶ ሕዝቡን መከተብ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
"ክትባቱን በማምረት ሂደቱ ላይ ግንኙነት የፈጠርነው ከአውሮፓ አገራትና እና ካናዳ ጋር ነው። ከጣልያን እና ፈረንሳይ የመጡ ተመራማሪዎችም በሂደቱ ላይ ይሳተፋሉ" ብለዋል ዶክተር ቪሴንቴ ቬሬዝ።
አክለውም "በሚያሳዝን ሁኔታ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የአሜሪካ ተሳትፎ የለም። ምናልባት ወደፊት በመሰል ሂደቶች ላይ ትብብር ሊኖረን እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።
እንደ ፓን አሜሪካን ሄልዝ ኦርጋናይዜሽን መሰል ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኩባ ለኮሮረናቫይረስ የሚሆነውን ክትባት በማግኘት የመጀመሪያዋ የላቲን አሜሪካ አገር እንደምትሆን ተስፋ ያደርጋሉ።
"ኩባ ክትባቱን እንደምታገኝ ተስፋ እናደርጋለን'' ይላሉ በኩባ የድርጅቱ ተወካይ ዶክተር ሆዜ ሞቫ። ''የሶብሬና 2 ክትባት ሁለተኛ ደረጃ ሙከራ ውጤትን ከሰማን በኋላ ሂደቱን በቅርበት ስንከታተለው ነበር። ካለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ኩባ የክትባቱን ውጤታማነትና ደኅንነት ስትመረምር እንደነበርም እናውቃለን።''
በአሁኑ ጊዜ በክትባቱ ዙሪያ ያለው ጉጉት ትልቅ ነው። በመጀመሪያ አገሪቱ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ ነው።
ወረርሽኙ በጀመረበት የመጀመሪያዎቹ ወራት ውስጥ በየቀኑ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ የነበረ ሲሆን ከብራዚልና ሜክሲኮ ጋር ሲነጻጸር ግን ቁጥሩ ብዙም አስፈሪ አይደለም። ነገር ግን የአገሪቱን የጤና ሥርዓት በእጅጉ ፈትኖታል።
ባሳለፍነው የአውሮፓውያኑ ዓመት አጋማሽ ላይ ኩባ የወረርሽኙን ስርጭት መግታት ችላ ነበር። በዋነኛነት አየር ማረፊያዎችን በመዝጋትና የማኅበረሰቡን እንቅስቃሴ በመገደብ ነበር ይህንን ማሳካት የቻለችው።
ሐምሌ እና ነሐሴ ላይ በጣም ዝቅተኛ የሚባል ስርጭትና ሞት ነበር የተመዘገበው።
የፓን አሜሪካን ሄልዝ ኦርጋናይዜሽን ተወካዩ በአሁኑ ጊዜ ያለው የቫይረሱ ስርጭት መቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለው ያስባሉ።
ነገር ግን ኩባ ውስጥ በወረርሽኙ ምክንያት በርካታ እንቅስቃሴዎች በመገደባቸው በጣም ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ መላሸቅ አጋጥሟታል። እንደውም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ከፍተኛው የኢኮኖሚ መድቀቅ ነው እየተባለ ነው።
ክትባቱ በአገር ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ደግሞ ሕዝቡን ከመክተብ ባለፈ ከሽያጭ ሊገኝ የሚችለው ገቢ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ሁኔታ ሊረዳው ይችላል ተብሎ ይታመናል። በተጨማሪም ከትባቱን ከሌሎች አገራት ማስመጣት ሊያስከትለው የሚችለውን ወጪ ይቀንሳል።
ኮሮረናቫይረስን ተከትሎ በኩባ በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ባለፈው ዓመት ብቻ ኢኮኖሚው 11 በመቶ ኪሳራ አጋጥሞታል። በተጨማሪም የምግብ ሱቆችና ሱፐር ማርኬቶች አካባቢ ከፍተኛ ሰልፍና ግፊያም ታይቷል።
በዚህ ወቅት ሁሉም ህጻናት ከትምህርት ቤት ቀርተዋል፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ ተቀዛቅዘዋል፣ የእንቅስቃሴ ገደቦችም ቢሆን የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አስቸጋሪ አድርጎታል። ስለዚህ የክትባቱ ዜና በርካቶች በጉጉት እንዲጠብቁት አድርጓቸዋል።
የዚህ ክትባት ውጤታማ መሆን የዜጎችን ጤንነት ከመጠበቅ ባለፈ ለጎረቤት አገራት ከሚደረገው ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ኢኮኖሚውን እንደሚያነቃቃው ይታመናል።