ሩሲያ ሠራሹ 'ሰፑትኒክ' ክትባት 92% ፈዋሽነቱ ተረጋገጠ

ሩሲያ ሠራሹ 'ስፑትኒክ' ተብሎ የሚጠራው የኮሮናቫይረስ ክትባት ፈዋሽነቱ በ92% በመቶ አስተማማኝ እንደሆነ ተረጋገጠ።

ይህ የተረጋገጠው ክትባቱን በ3ኛ ምዕራፍ ሰፊ ጥናት የተሳተፉ ሰዎችን ሁኔታ በማየት በታተመ ሳይንሳዊ ትንታኔ ነው።

የዚህ የሦስተኛ ምዕራፍ ውጤት በታዋቂው ላንሴት የጤና ጆርናል ላይ ታትሞ ወጥቷል።

ክትባቱ በበርካታ ሰዎች ላይ ከተሞከረ በኋላ ክትባቱ የተሰጣቸው ሰዎች ከተለመዱት መለስተኛ የህመም ምልክቶች ሌላ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላመጣባቸው ተስተውሏል።

ስፑትኒክ ክትባት ጤንነትን የማይጎዳና ለተህዋሲው አስተማማኝ መከላከልን የሚሰጥ እንደሆነ ተረጋግጦለታል።

ይህ ክትባት ከሌሎች ክትባቶች በተለየ ቀደም ብሎ በሩሲያ መሰጠት መጀመሩን ተከትሎ በቂ ጥናትና ምርምር ሳይደረግበት ነው ለሕዝብ የታደለው በሚል ጭቅጭቅ አስነስቶ እንደነበር ይታወሳል።

ብዙ የምዕራብ አገራትም ለሩሲያ ሠራሹ ክትባት ዕውቅና ነፍገውት ቆይተዋል።

አሁን ግን ሳይንቲስቶቹ አስተማማኝነቱን አረጋግጠናል ብለዋል።

ይህን ተከትሎም ሩሲያ ሠራሹ ስፑትኒክ ክትባት በዓለም እውቅና የተሰጣቸውን 4 ክትባቾን ተከትሎ 5ኛ ሆኖ ተመዝግቧል።

አራቱ ዋንኛው የኮቪድ ክትባቶች ፋይዘር፣ ኦስክስፎርድ አስትራዜኒካ፥ ሞደርና እና ጃንሰን ናቸው። አሁን ሰፑትኒክ ይህንኑ ተርታ ተቀላቅሏል።

ስፑትኒክ ክትባት የሚሰራበት መንገድ ልክ እንደ በታላቋ ብሪታኒያ ውስጥ እንደተመረተው ኦክስፎርድ አስትራዜኒካ እና በቤልጂየም እንደተሰራው ጃንሰን ነው።

ይህም ማለት ክትባቱ የሚጠቀመው ደካማ ተህዋሲውን ሲሆን ይህ ተህዋሲ በቤተ ሙከራ ውስጥ በምህንድስና ይበልጥ እንዲዳከም ከተደረገ በኋላ ሰውነት ለዚህ ደካማ ተህዋሲ እንዲጋለጥ የማድረግ ዘዴ ነው።

በጥንቃቄ ደካማውን የተህዋሲውን ዝርያ ለሰውነት በማጋለጥና ጄኔቲክ ኮዱን ሰውነት እንዲያውቀው በማድረግ ሰውነት በሽታውን አውቆ እንዲዋጋው የማድረግ ጥበብ ነው።

ይህን ክትባት የወሰደ ሰው ሰውነቱ ወዲያውኑ አንቲቦዲ ተከላካዮችን ያመርታል።

ይህ ስፑትኒክ ክትባት ከ2 እስከ 8 ዲግሪ ሴንትግሬድ ውስጥ ሊቀመጥ ስለሚችል ለማጓጓዝ የተሻለ ክትባት ሆኖ ተወስዷል።

ይህም ክትባቱ እንደ ፋይዘር ለማጓጓዝም ሆነ ለማጠራቀም የተለየ ማቀዝቀዣ ስለማይፈልግ ነው።

ስፑትኒክ ክትባትን ሌላ ልዩ የሚያደርገው 2 ጊዜ በ21 ቀናት የሚሰጡት ክትባቶች በተወሰነ ደረጃ መለያየታቸው ነው። ይህም ሰውነት ተህዋሲውን በደንብ እንዲለየው ለማድረግ ነው ተብሏል።

ስፑትኒክ ክትባት ከሩሲያ ሌላ በአርጀንቲና፥ በፍልስጤም ግዛቶች፣ በቬንዝዌላ፥ በሐንጋሪ፥ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና በኢራን አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው።