ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቢሊየነሩ ጄፍ ቤዞስ ከአማዞን ሥራ አስፈጻሚነቱ ሊለቅ ነው
የአማዞን መሥራችና ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ከኩባንያው ሥራ አስፈጻሚነት እንደሚለቅ አስታወቀ።
ቤዞስ ከ30 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ አምጦ የወለደውን ድርጅቱን የሚለቀው ሌሎች ሥራዎች ላይ ለማተኮር በማሰቡ ነው።
ሆኖም ከአማዞን የዕለት ተዕለት ሥራ አስፈጻሚነት ቢለቅም የበላይ ጠባቂ ሆኖ መሥራቱን አይተውም።
'እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት ጊዜዬንና ጉልበቴን ሌሎች ሥራዎች ላይ ለማድረግ ስለፈለኩ ነው' ብሏል ቢሊየነሩ ጄፍ ቤዞስ።
የዓለም ቢሊየነሩን ቤዞስን በሥራ አስፈጻሚነት የሚተኩት አንዲ ጄሲ ይሆናሉ። አንዲ የአማዞንን ክላውድ ኮምፒውቲንግ ቢዝነስ ክፍል ኃላፊ ሆነው የቆዩ ናቸው።
ጄፍ ቤዞስ ከሥራ አስፈጻሚነቱ በይፋ የሚለቀው በዚህ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት አጋማሽ ይሆናል።
'የአማዞን ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ መሥራት ፋታ የለውም። ጊዜና ጉልበትን ያሟጥጣል። እንዲህ ዓይነት ኃላፊነት ላይ መሆን ሌሎች ነገሮች ላይ ለማተኮር ጊዜ አይሰጥም' ይላል ቤዞስ በይፋ በጻፈው የመልቀቂያ ደብዳቤ።
'እንደ በላይ ጠባቂ ሆኜ በዋና ዋና የአማዞን ጉዳዮች ብቻ እየተሳተፍኩ ትኩረቴን ግን ለሌሎች ድርጅቶቼ መስጠት እፈልጋለሁ' ብሏል በዚሁ ደብዳቤ ቤዞስ።
ቢሊየነር ቤዞስ አሁን ትኩረት ሊያደርግበት የፈለጋቸው የሥራ ዘርፎች በህዋ ትራንስፖርት ላይ የሚያተኩረው ብሉ ኦሪጂን እንዲሁም ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ህትመት እና ሌሎች የግል ፍላጎቶቹ ላይ ነው።
'በፍጹም ጡረታ እየወጣሁ አይደለም፤ ጉልበቴና የመንፈስ ጥንካሬዬ አሁንም እንዳለ ነው፤ ነገር ግን ትኩረቴን ሌሎች ነገሮች ላይ ለማዋል ስለፈለኩ ብቻ ነው' ብሏል ቤዞስ በዚሁ ደብዳቤው።
ቢሊየነሩ ቤዞስ አሁን 57 ዓመቱ ነው።
የአማዞን የበይነ መረብ ገበያን የጀመረው በ1994 ሲሆን ያን ጊዜ መጽሐፍ በበይነ መረብ የሚሸጥ ትንሽ ድርጅት ሆኖ ነበር አማዞን የተመሰረተው።
አሁን አማዞን በመላው ዓለም 1.3 ሚሊዮን ሰራተኞች አሉት። በ2020 ዓ/ም ብቻ የአማዞን ጠቅላላ ሽያጭ 386 ቢሊዮን ዶላር አልፏል። ይህም የሆነው በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የበይነ መረብ ገበያው ስለደራ ነው።
ጄፍ ቤዞስ በፎርብስ የሀብት ዝርዝር ውስጥ የተጠቀሰለት ሀብቱ 192 ቢሊዯን ዶላር ደርሷል።