በፈረንሳይ ሰልፍ ላይ ጥቃት ሊያደርስ ነበር የተባለው የኢራን ዲፕሎማት እስር ተፈረደበት

በግዞት ያሉ የኢራን ተቃዋሚ ቡድኖች በፈረንሳይ ባደረጉት ሰልፍ ላይ የቦንብ ጥቃት ለመፈፀም አሲሯል የተባለው የኢራን ዲፕሎማት የእስር ቅጣት ተበይኖበታል።

በወቅቱ ኦስትሪያ፣ ቪየና ይገኝ በነበረው የኢራን ኤምባሲ ይሰራ ነበር የተባለው አሳዶላህ አሳዲ የቤልጂየሙ ፍርድ ቤት የ20 አመት እስር ፈርዶበታል።

ከአውሮፓውያኑ 1979 የኢራን አብዮት በኋላ በአውሮፓ ህብረት የተከሰሰ የመጀመሪያው የኢራን ባለስልጣን ሆኗል- የ49 አመቱ አሳዶላህ አሳዲ

ከሱ በተጨማሪ ሶስት ሌሎች ተጨማሪ ሰዎችም ተፈርዶባቸዋል። ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የጀርመን፣ ፈረንሳይና ቤልጂየም ፖሊሶች ጥምር ኃይል ባደረጉት ዘመቻ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2018 በፈረንሳይ ከፓሪስ ወጣ ብላ በምትገኝ ስፍራ በተደረገው ሰልፍ የዶናልድ ትራምፕን ጠበቃ ሩዲ ጁሊያኒን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚገኙ ሰዎች የታደሙበት ነበር ተብሏል።

ፈረንሳይ ታስቦ የነበረው ጥቃት የተቀነባበረ ነው ከጀርባውም የኢራን ደህንነት ሚኒስቴር አለበት በማለት የምትወነጅል ሲሆን የሁለት ኢራናውያን ባለስልጣናትን ንብረትም እንዳይንቀሳቀስ አድርጋለች።

ኢራን በበኩሏ የተባለው ጥቃት የተፈጠረ ሴራ ነው ትላለች።

" ይህ ውሳኔ ሁለት ነገሮችን አሳይቷል። አንደኛው ለወንጀል ተግባራት ሲሆን ማንኛውም ዲፕሎማት ያለመከሰስ (ያለመጠየቅ መብቱ) እንደሚገረሰስና ሁለተኛው ደግሞ የበርካታ ሰዎች ህይወትን ሊቀጥፍ የሚችለውን ጥቃት የኢራን ኃላፊነት እንደሆነ" በማለት አቃቤ ህግ ሄንሪ ቢየውቲየር ለሮይተርስ ተናግረዋል።

በጥቃቱ ኢላማ ነበሩ የተባሉትና በግዞት ላይ ያለው የናሺናል ካውንስል ኦፍ ሬዚስታንስ ኦፍ ኢራን (NCRI) መሪ ማርያም ራጃፊ ውሳኔውን "ለኢራን ህዝብና እየታገለ ላለው ትልቅ ድል ነው። ለኢራን መንግሥት ደግሞ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራ ነው" ብለዋል።

ኤንሲአርአይ በኢራን መንግሥት የሽብርተኛ ቡድን ተብሎ የተፈረጀ ሲሆን የእስላሚክ ሪፐብሊክ እንዲገረሰስ የሚሰራ ቡድን ነው።