መንግሥት በትግራይ ተፈጸሙ የተባሉ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚመረምር ግብረ ኃይል አቋቋመ

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ተፈጽመዋል የተባሉ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚመረምር ግብረ ኃይል መቋቋሙ ተገለጸ።

በፌደራሉ መንግሥት የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከጤና ሚንስቴር፣ ከሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚንስቴር፣ ከአገር መከላከያ እና ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተወጣጡ አባላትን ያካተተ ነው።

ከሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚንስቴር ሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ አድነው አበራ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ እንደተናገሩት የተቋቋመው ግብረ ኃይል መቀሌ መግባቱን እና የምርመራ ሥራውን ጀምሯል።

ከፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ተደጋጋሚ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየደረሱ ስለመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሪፖርት ሲደርሳቸው መቆየቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

በተባበሩት መንግሥታት በግጭቶች ውስጥ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚከታተሉት ፕርሚላ ፓተን፤ ጥር 14 2013 የቤተሰብ አባላታቸውን ተገደው እንዲደፍሩ የተደረጉ ግለሰቦች ስለመኖራቸው የሚረብሹ ሪፖርቶች ደርሰውናል ብለው ነበር።

ፕራሚላ፤ መሠረታዊ ቁሶችን ለማግኘት ሲባል ከወታደሮች ጋር ወሲብ ለመፈጸም የሚገደዱ ሴቶች ስለመኖራቸው፣ ድንገተኛ የእርግዝን መከላከያ መድሃኒቶችን የሚፈልጉ ሴቶች ቁጥር ስለመጨመሩ እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎችም በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚያትቱ ሪፖርቶች ጨምረዋል ማለታቸው ይታወሳል።