ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና ይቅርብኝ ያለችውን የአውስትራሊያ ወይን እንግሊዞች እየሸመቱት ነው
ከአውስትራሊያ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እየገባ ያለው የወይን ምርት መጠን 30 በመቶ ጨምሯል።
ቻይና ከአውስትራሊያ ጋር በገባችው ጠብ ምክንያት የወይን ምርቶች ላይ የጫነችውን ቀረጥ ተከትሎ አምራቾች ገበያ አጥተው ነበር።
ቻይና የወይን ምርቶቹ ላይ የጫነችው ቀረጥ 212 በመቶ ሲሆን ሎብስተር የተሰኘው የባሕር እንስሳ ስጋና የድንጋይ ከሰል ቀረጥ የተጫነባቸው ምርቶች ናቸው።
ነገር ግን ባለፉት 10 ዓመታት ታይቶ በማይውቅ ሁኔታ የአውስትራሊያ ወይኖች በአውሮፓ ገበያቸው ደርቷል።
ዋይን አውስትራሊያ የተሰኘው ተቋም የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች የአውስትራሊያ ወይን የጣፈጣቸው በእንቅስቃሴ ገደብና በብሬግዚት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ይላል።
አውስትራሊያ ወደ አውሮፓ የምትልከው የወይን ምርት ከባለፈው ዓመት ሲነፃፀር ዘንድሮ 22 በመቶ አድጎላታል።
ከአውሮፓ ሃገራት ደግሞ ዩኬ ቀንደኛዋ ገዥ ሆናለች።
የአውስትራሊያ መንግሥት የወይን ኢንዱስትሪውን ለማስተዋወቅ ደፋ ቀና እያለ ነው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የወይን ምርቶች ገበያ እንዲደራ ምክንያት እንደሆነ ዋይን አውስትራሊያ ይናገራል።
አልፎም በብሬግዚት ወቅት በርካታ ሰው ወይን እንደሸመተ ድርጅቱ ያለው መረጃ ያሳያል።
ቻይና የአውስትራሊያ ወይኖችን በገፍ የምታስጭን ሃገር ነበረች።
ከአውስትራሊያ የወይን ምርቶች 39 በመቶውን በማስገባትም ከዓለም ቀዳሚዋ ሃገር ነበረች።
አሁን ግን ዩኬ ይህን ስፍራ ተረክባለች።
ብሪታኒያዊያን ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2020 ብቻ 266 ሚሊዮን ጠርሙስ የአውስትራሊያ ወይን ጠጥተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአውስትራሊያ ቀይ ወይን 57 በመቶ የወይን ሽያጭን ይሸፍናል።
ቻይናና አውስትራሊያ ያላቸው ፍጥጫ ከፖለቲካ አልፎ ወደ ንግድ ገብቷል።
ቻይና በአውስትራሊያ የወይን ምርቶች ላይ ቀረጥ ከፍ ያደረግኩት በፖለቲካዊ አለመግባባት ምክንያት አይደለም ስትል ትከራከራለች።
አውስትራሊያ ግን ይህን አትቀበልም።
አውስትርራሊያ ወደ ቻይና የምትልካቸው ምርቶች መጠን 14 በመቶ የቀነሱ ሲሆን ይህን 1 ቢሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ይገመታል።