ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ እና ሩሲያ፡ ሁለቱ ኃያላን ሃገራት የኒውክሌር ስምምነታቸውን አራዘሙ
አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ያላትን የኒውክሌር መሣሪያ ቁጥጥር ስምመነት ለአምስት ዓመታት አራዘመች።
ስምምነቱን ይፋ ያደረጉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን "ስምምነቱ ዓለምን የበለጠ ሰላም አድርጓል" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ከሳምንት በፊት በስልክ ማውራታቸው ሲነገር ነበር።
አርብ ዕለት ደግሞ ስምምነቱ ሕግ ሆኖ እንዲጸድቅ ፈርመውበታል ተብሏል። ስምምነቱን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለማራዘም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከነገ ወዲያ ጥር 28 ያበቃ ነበር።
ሆኖም ግን አዲሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስምምነቱን ለማራዘም ተስማምተዋል። ስምምነቱን ቻይናም ትቀላቀለዋለች ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን ጠንከር ያሉ መስፈርቶችንና ሂደቶችን ከማለፉም በተጨማሪ አንዳንድ 'ታክቲካል' የጦር መሣሪያዎችንም ያካትታል ተብሏል።
'ስትራቴጂክ የጦር መሣሪያ ቅነሳ ስምምነት' ተብሎ የሚጠራው ስምምነቱ፣ በአሜሪካ እና ሩሲያ መካከል የቀረው የመጨረሻው የኒውክሌር ስምምነት ነው። የመጨረሻ መዳረሻውም ሁሉንም የኒውክሌር መሣሪያዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረግ ነው።
"የአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ የጦር መሣሪያ ቅነሳ ስምምነት መራዘም አሜሪካን እና ዓለምን ደኅንነታቸው የተጠበቀ ያደርጋል" ብለዋል የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው።
"ይህ የሚያሳየው ጦርነት የመከሰትን እድል የሚቀንሰውን ውጤታማ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር የሚያደርግ እና የመሣሪያ ውድድርን የሚያስቀር ነው" ብለዋል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መግለጫ ደግሞ በሞስኮ የአሜሪካ ኢምባሲ የስምምነቱ ልውውጥ ከተካሄደ በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ብሏል። ስምምነቱም የፊርማ ሂደቱ ከተጠናቀቀ ጊዜ ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚውል ተገልጿል።
በፈረንጆቹ 2010 የተደረሰው ስምምነት ሁለቱ ሃገራት በነብስ ወከፍ ከ1550 በላይ የረዥም ርቀት ተጓዥ ኒውክሌሮች እንዳያከማቹ ያግዳል።
ሁለቱ ሃገራት ከ700 በላይ ባለስቲክ፣ የባህር ባለስቲክ እና ከባድ ቦምብ ጣይ መሣሪያዎች በተለያዩ ክፍለ ዓለማት እንዳያከማቹ ስምምነቱ ያግዳቸዋል።
ሩስያ በርካታ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ክምችት ያላት የዓለማችን ሃገር ናት። የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ፌደሬሽን የተሰኘው ተቋም ሩስያ 6500 የኒውክሌር መሣሪያዎች እንዳላት ይገመታል።
አሜሪካ ደግሞ በ6 ሺህ 185 የኒውክሌር መሣሪያዎች ብዛት ሁለተኛ ናት። ሶስተኛ ፈረንሳይ [300]፤ አራተኛ ቻይና [290]፤ አምስተኛ ዩኬ [215] በመሆን ተቀምጠዋል። ሰሜን ኮሪያ ከ20-30 የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳላት ይገመታል።