በኢራን የኒውክሌር ማዕከል ላይ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ደረሰ

ኢራን ውስጥ በሚገኝ አንድ ዋነኛ በተባለ የኒውክሌር ተቋም ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ "ከባድ ጉዳት" መድረሱን የአገሪቱ ኒውክሌር ኃይል ተቋም ቃል አቀባይ አረጋገጡ።

ናታንዝ በተባለው የኒውክሌር ማብላያ ማዕከል ላይ ለደረሰው የእሳት አደጋ ምክንያቱ መታወቁን የገለጹት ቃል አቀባዩ ነገር ግን ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥበዋል።

ጨምረውም በአደጋው የወደሙት የማዕከሉ ማሽኖች እጅግ ዘመናዊ በሆኑ አዲስ መሳሪያዎች መቀየራቸውንም ተናግረዋል።

በኒውክሌር ማብላያው ቁልፍ ክፍል ላይ ለተነሳው የእሳት አደጋ የመረጃ መረብ አሻጥር (የሳይበር ጥቃት) ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው መሳሪያዎች ኒውክሌር ኃይል እና ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ የሚውል የዳበረ ዩራኒየም ለማዘጋጀት የሚያገለግል ነው።

የኢራን አውቶሚክ ኃይል ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት ቤህሩዝ ካማልቫንዲ እሁድ እንደተናገሩት የአገሪቱ የደኅንነት ባለስልጣናት በናታንዝ የኒውክሌር ማዕከል ላይ ስለደረሰው የእሳት አደጋ ያልተናገሩት "በደኅንነት ምክንያት" ነው ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አደጋው "ከፍተኛ ጉዳትን ቢያደርስም፤ በሰው ላይ ግን የደረሰ ጉዳት የለም" ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ኢራን ውስጥ የተለያዩ የእሳት አደጋዎችና ፍንዳታዎች አጋጥመው እንደነበረም ተገልጿል።

ካማልቫንዲ ጨምረው "አደጋው በአጭር ጊዜ ውስጥ በማዕከሉ የዩራኒየም ምርት ሥራን ላይ መዘግየትን ሊያስከትል ይችላል። ኢራን በእሳቱ ጉዳት የደረሰበትን ህንጻ በትልቅና ዘመናዊ ማዕከል ትተካዋለች" ሲሉ የተያዘውን እቅድ አሳውቀዋል።