ዘረኛ ቃል የተጠቀመው አሜሪካዊው ዘፋኝ ወቀሳ ቀረበበት

አሜሪካዊው የሐገረሰብ ሙዚቃ ኮከብ ጥቁሮችን የሚያንቋሽሽ ቃል ሲጠቀም የሚያሳይ ምስል መውጣቱን ተከትሎ ወቀሳ እየደረሰበት ነው።

ሞርጋን ዋለን የተሰኘው ሙዚቀኛ ወኪል የሆነው ቢግ ላውድ ሪከርድስ የተሰኘው ተቋም ከሙዚቀኛው ጋር ያለውን ውል መቅደዱን አሳውቋል።

ባለፈው ሳምንት በዘፋኙ ጎረቤት የተቀዳ ነው በተባለው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ዘፋኙ ጓደኞቹን ሲሰናበትና አንደኛውን ባልንጀራውን 'ኒ**' ብሎ ሲጠራው ይሰማል።

ዘፋኙ በዚህ ድርጊቱ እንደተፀፀተ በማሳወቅ ይቅርታ ጠይቋል።

"በድርጊቴ አፍሪያለሁ፤ ይቅርታም እጠይቃለሁ" ሲል ቲኤምዚ ለተሰኘውና ተንቀሳቃሽ ምስሉን ላተመው ጣቢያ ቃሉን ሰጥቷል።

"ተቀባይነት የሌለው ዘረኛ ቃል ተጠቅሚያለሁ። ወደኋላ ተመልሼ ይህን ፀያፍ ድርጊቴን ብሰርዘው ምንኛ ደስ ባለኝ። ይህንን ቃል ለመጠቀምምክንያት መደርደር አይጠበቅብኝም። ይህንን በማድረጌ ከልቤ ይቅርታ ልጠይቃችሁ እወዳለሁ። ከዚህ የተሻለ ሰው መሆኔን ማሳየት እሻለሁ" ብሏል ዘፋኙ በይቅርታው።

ዘ ቮይስ በተሰኘው የሙዚቃ ውድድር ላይ ቀርቦ የተመልካቾችን ቀልብ በመግዛት ወደ ዝና የተስፈነጠረው ዋለን፤ አሜሪካ ውስጥ አሁን አሉ ከሚባሉ የሐገረሰብ ሙዚቃ አቀንቃⶉች መካከል አንዱ ነው።

'ዴንጀረስ' ሲል የሰየመው የመጨረሻው አልበሙ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ራድዮኖችን አጠለቅልቆ ነበር።

ለመጨረሻ ጊዜ የለቀቃቸው አራት ነጠላ ዜማዎቹም ተወዳጅነታቸው ናኝቶ ቆይቷል።

ነገር ግን ሰውዬው ዘረኛ ቃል መጠቀሙ ይፋ ከሆነ በኋላ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አንቅሮ ተፍቶታል።

ምስሉ በተለቀቀ በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ በአሜሪካ ትልቁ የራድዮ ጣቢያዎች ድርጅት የተባለው አይኸርትራድዮ የዋለን ሙዚቃ ላለማጫወት ቃል ገብቷል።

አይኸርትራድዮ 850 ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከል 135ቱ በዋናነት የሐገረሰብ ሙዚቃ የሚያጫውቱ ናቸው።

ሌሎችም ግዙፍ ድርጅቶች የሙዚቀኛው ነገር በቃን ብለዋል።

የራድዮ ጣቢያዎች ብቻ ሳይሆን ቴሌቪዥኖችም የሙዚቀኛውን ሥራዎች ላለማጫወት ወስነዋል።

የበይነ መረብ ሙዚቃ አጫዋች ድርጅቶችም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል።

ስፖቲፋይ የተሰኘው የኢንተርኔት ሙዚቃ አጫዋች እንዲሁም ቱደይስ ካንትሪ የዋለን ሙዚቃ ከማሕደራቸው ሰርዘዋል።

ሙዚቀኛው ከወኪሉ ጋር የነበረው ፊርማ መቀደዱን አስመልክቶ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

ዋለን ለመሰል ግርግር ብርቅ አይደለም።

ባለፈው ግንቦት አንድ መሸታ ቤት ገብቶ ሰክሮ ግርግር በመፍጠሩ ለእሥር ተዳርጎ ነበር።

በጥቅምት ወር ደግሞ የኮቪድ-19 ሕግን ጥሶ በመገኘቱ በእንግድነት ከተጋበዘበት አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ እንዳይገኘ ሆኗል።