የዓለም ምግብ ድርጅት የአንበጣ መከላከያ ርጭት ለማካሄድ የገንዘብ እጥረት ገጥሞኛል አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ድርጅት (ፋኦ) በምስራቅ አፍሪካ የአንበጣ ወረርሽኝን ለመዋጋት ያሰማራቸውን አውሮፕላኖች ሙሉ በሙሉ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሊያቆማቸው እንደሚችል አስጠነቀቀ።
የዓለም ምግብ ድርጅት እንዳለው ከሆነ አውሮፕላኖችን ለማንቀሳቀስ 38 ሚሊዮን ዶላር ይፈልጋል።
አዲስ የአንበጣ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ ተከስቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ገበሬዎችን ሕይወት ፈተና ውስጥ መጣሉ ተልጿል።
እነዚህ በአንበጣ ወረርሽኝ የተጎዱ አካባቢዎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም በከባድ ጎርፍ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።
እንደ ፋኦ ምዘና ከሆነ በኬንያ ብቻ በ11 ግዛቶች የአንበጣ ወረርሽኝ የተከሰተ ሲሆን መንጋው ወደ ታንዛንያ የባህር ዳርቻዎች እየተመመ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ሰፊ የሆነ የእርሻ ማሳ በአንበጣ ወረርሽኝ የተነሳ መውደሙም ተገልጿል።
በምስራቅ አፍሪካ በዚህ ዓመት ብቻ የአንበጣ ወረርሽኝ ሲከሰት ሶስተኛው ነው።
አዲሱ የአንበጣ ወረርሽኝ የተራባው በሳይክሎን ጋቲ ታግዞ ሲሆን፣ በቀጠናው በአንድ ጊዜ የሁለት ዓመት ዝናብ በአጭር ቀናት ውስጥ አስከትሎ ነበር።
ይህ ደግሞ ለአንበጣ መንጋ መራቢያነት ምቹ ሆኖ ማገለገሉን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሶማሊያ የዓለም ምግብ ድርጅት የድንገተኛ እርዳታ ማስተባባሪያ ኃላፊ የሆኑት ኢዛና ካሳ "የወረርሽኙ ተጽዕኖ ከዚህ ቀደምም ደካማ የምግብ ዋስትና የነበረው አርሶ አደር፣ ከፊል አርብቶ አደር እንዲሁም አርብቶ አደሩ ሕይወት ላይ፣ የበለጠ ጫና ያሳድራል።" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው ከሆነ ከባለፈው ዓመት ታሕሳስ ወር ጀምሮ በመሬት እና በአየር የሚደረገው የፀረ ተባይ መድሃኒት ርጭት 1.2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ምግብ እና የወተት ተዋጽኦ ከውድመት ታድጓል።
"አፍሪካ ከዚህ ቀደም በዚህ መጠን የአንበጣ ወረርሽኝ ያየችው፣ በሳህል አካባቢ ሲሆን፣ ሙሉ በሙለ ለመቆጣጠርም ሁለት ዓመት እና 500 ሚሊዮን ዶላር ያህል ያስፈልጋል።"
የዓለም ምግብ ድርጅት (ፋኦ) ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል ላውረንት ቶማስ "ይህ ወረርሽኝ በጣም ከፍተኛው ነው፣ ነገር ግን በምስራቅ አፍሪካ ለመቆጣጠር ቁርጠኝነቱ አለ። መንግሥታት እነዚህ አውሮፕላኖች መብረር እንዲችሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።"















