ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶናልድ ትራምፕ በስንብት ንግግራቸው ምን አሉ?
ከ12 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተብለው የሚጠሩት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው የስንብት ንግግር አድርገዋል።
ይህ ንግግራቸው የተሰራጨው በዩትዩብ ነው።
"ለማድረግ ያሰብነውን አድርገናል፣ ከዚያም በላይ ነው ያሳካነው" ብለዋል ትራምፕ በንግግራቸው።
"ከባዱን አውደ ውጊያ ላይ ነበር የተሳተፍኩት፣ ከባድ ፍልሚያ ነው ያደረኩት፤ ምክንያቱም የመረጣችሁኝ ያን እንዳደርግ ስለነበረ" ብለዋል ትራምፕ።
ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው በጆ ባይደን መሸነፋቸውን ሙሉ በሙሉ አልተቀበሉትም።
46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላ ለመፈጸም ሰዓታት ብቻ የቀሯቸው ጆ ባይደን በበኩላቸው በኮቪድ ተህዋሲ ለሞቱ 400 ሺህ አሜሪካዊያን የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
400 ሻማዎች በሊንኮን ሜሞሪያል ግቢ ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ በርተዋል፤ በተህዋሲው የሞቱትን ዜጎች ለማሰብ።
የትራምፕ የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው የማይደፈረውን ካፒቶል ሒልን በመድፈራቸው በነውጥ የታጀበ ጊዜ ሆኖ ነበር የቆየው።
የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን የደፈሩት በመሪያቸው በፕሬዝዳንት ትራምፕ ተገፋፍተው ስለነበር ትራምፕ ለ2ኛ ጊዜ ለመከሰስ በቅተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በንግግራቸው አንድም ቦታ ላይ ጆ ባይደንን በስም አልጠሩም።
ሆኖም ፖለቲካዊ ብጥብጥና ነውጥ የአሜሪካ ባህል አይደለም፤ አንታገሰውም ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ ነውጥ በማስነሳታቸው ክሳቸው መታየት ይቀጥልና ጥፋተኛ ከሆኑ ለሌላ ጊዜ ለየትኛውም የአሜሪካ ሥልጣን እንዳይወዳደሩ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ በሥልጣን ላይ ሳለ ለ2ኛ ጊዜ የተከሰሰ ብቸኛው ፕሬዝዳንት ነው የሚሆኑት።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ አሜሪካ ትኩረቷን ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ልታነሳ አልቻለችም። በዚህ መሀል ግን 24 ሚሊዮን ዜጎቿ በተህዋሲው ተይዘው 400ሺህ መሞታቸውን ልብ ያለ እምብዛም ነው።
በተህዋሲው መዛመት የመጀመርያ ጊዜያት ትራምፕ ይህ ወረርሽኝ ጉንፋን ነው በራሱ ጊዜ ይጠፋል ሲሉ ያጣጥሉት እንደነበር አይዘነጋም። አማካሪዎቻቸውም ቢሆኑ ወረርሽኙ የ400ሺህ ዜጎችን ሕይወት ሊቀጥፍ ይችላል ብለው አልገመቱም ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ በስንብት ንግግራቸው በአሜሪካ ታሪክ እጅግ አይበገሬውን ምጣኔ ሀብታዊ ስኬት አስመዝግበናል፤ ይህም በዓለም አንደኛና ትልቁ ነው ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት የስንብት ንግግር በሚቀጥለው ሕይወታቸው ምን እንደሚያደርጉ ፍንጭ አልሰጡም።
ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎቼ ብዙ ናቸው፤ እኔ ተወዳጁ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነኝ ሲሉ በተደጋጋሚ ቢናገሩም በዚህ ወቅት በአሜሪካ ያላቸው የይሁንታና ተሰሚነት ምጣኔ አሽቆልቁሎ 34 ፐርሰንት መድረሱ ተዘግቧል።
ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ረቡዕ ማምሻውን (በምሥራቅ አፍሪካ አቆጣጠር)፣ ቀትር ላይ (በምሥራቃዊ አሜሪካ አቆጣጠር) ከዋይት ሐውስ ይወጣሉ። ጆ ባይደን ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ግን ትራምፕ አይገኙም።