ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ነውረኛ ኬኮችን ጋግረሻል" የተባለችው ግብጻዊት በቁጥጥር ስር ዋለች
ግብጽ ውስጥ "ነውረኛ ኬኮችን ጋግረሻል" የተባለች ሴት ለአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ውላ መለቀቋን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
ኬኮቹ በመራቢያ አካልና በሙታንታ ቅርጽ ተሰርተው ክሬም የተዘጋጁ ሲሆኑ ለልደት ክብረ በዓል በካይሮ ስፖርት ክለብ ውስጥ የቀረቡ ናቸው ተብሏል።
የእነዚህ ኬኮች ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በርካቶች ከተቀባበሉት በኋላ፣ የጋገረችው ሴት በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን በኋላም 319 ዶላር ለዋስትና በማስያዝ ከእስር ወጥታለች። በዚህ የልደት ድግስ ላይ የተሳተፉ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል እየተባለ ነው።
አንድ ከፍተኛ የሐይማኖት አባት በእንዲህ አይነት ቅርጽ የሚጋገሩ ነገሮች በእስልምና የተከለከሉ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።
ዳር አል-ኢፍታ የተባሉ ሰው ደግሞ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ እንደጻፉት እንዲህ አይነት ከወሲባዊ ነገሮችን የሚወክሉ ነገሮች "የማኅበረሰብ እሴትን የሚያንቋሽሹ እና ማኅበረሰቡን መናቅ ናቸው" ብለዋል።
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ በክለቡ ውስጥ ድግሱን ያዘጋጁ እና ድግሱ ላይ የተሳተፉ ሰዎችን እየፈለገ ነው ተብሏል።
የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ኔጋድ ኤል ቦራይ በትውተር ሰሌዳቸው ላይ "የተወሰነ የማኅበረሰብ ክፍል በመንግሥት እየታገዘ የግብጻውያንን ቤተሰባዊ እሴቶች ለመጠበቅ በሚል የግል ነጻነትን ለመደፍጠጥ ይፈልጋል" ሲሉ ጽፈዋል።
ከዚህ ቀደም በርካታ ወጣት ግብጸውያን በቲክቶክና ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምስል የተነሳ ግብረገብነትን በመጣስ መወንጀላቸውንም አስታውሷል።
ባለፈው ማክሰኞ፣ "የቤተሰብ እሴትን ዝቅ ያደረገ" እና "ተገቢ ያልሆነ" ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለጥፈዋል በሚል የተከሰሱ የሁለት ወጣት ሴቶችን ክስ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል።
ነገር ግን ከቀናት በኋላ ሃናን ሆሳም እና ማውዳ አልአድሃም የተባሉት ተከሳሾችን ዐቃቤ ሕግ እንዳይለቀቁ በማለት በሕገወጥ የሰው ዝውውር እፈልጋቸዋለሁ ብሏል።
ዐቃቤ ሕግ እነዚህ ተከሳሾች ታዳጊ ልጆችን ከእነርሱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ተንቀሳቃሽ ምስል እንዲለጥፉ አበረታተዋል ብሏል።
የሴቶቹ ጠበቆች ይህንን የዐቃቤ ሕግ ውሳኔን ይግባኝ እንደሚሉ አስታውቀዋል።