ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በታይላንድ ንጉሥን ተችተሻል የተባለች ሴት 43 ዓመት ተፈረደባት
አንዲት የታይ ሴት የንጉሣዊያኑን ቤተሰብ ተችተሻል በሚል 43 ዓመት እስራት ተፈርዶባታል።
በአገሪቱ ታሪክ ንጉሥን ለተቸ ይህ ትልቁ የእስር ውሳኔ ነው ተብሏል።
አንቻን የሚል ስም ያላት ይቺ ሴት በማኅበራዊ ሚዲያ የድምጽ ፖድካስቶችን ነበር ከ7 ዓመታት በፊት ለሕዝብ ያጋራችው።
እሷ እንደምትለው እነዚህን ንጉሡን የሚተቹ የድምጽ ፋይሎች ዝምብላ ከማጋራት ውጭ ያደረገችው ነገር የለም።
የታይላንድ 'ልሴ ማጄስቴ' ሕግ በዓለም ላይ ጥብቅ ከሚባሉት ሕጎች የሚመደብ ሲሆን በፍጹም ንጉሣዊያን ቤተሰቡን በማንኛውም ሁኔታ፣ ምንም ቢያደርጉ መተቸት ወይም ማጥላላት ወይም ነቀፋ መሰንዘርን ይከለክላል።
ታይላንድ የንጉሣዊ ዲሞክራሲ ሥርዓትን የምትከተል አገር ስትሆን ይህ እንዲለወጥ በቅርብ ጊዜ ወጣቶች አደባባይ ወጥተው በመቃወማቸው ከፖሊስ ጋር ተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል።
ተከሳሽ አንቻን ንጉሡን የሚተቹ ድምጾች ያሉበትን ይዘት ከ2014 እስከ 2015 በዩትዩብና በፌስቡክ ስታጋራ በመቆየቷ 29 ክሶች ተከፍቶባት ስትከራከር ነበር።
አንቻም የማይከሰሱትን፣ የማይገረሰሱትን ፍጹማዊውን ንጉሥ ተዳፍራችኋል በሚል ከተከሰሱ 14 ሰዎች አንዷ ናት።
አንቸም መጀመርያ ድርጊቱን በመፈጸሟ የተፈረደባት የ87 ዓመት እስር የነበረ ሲሆን የቅጣት ማቅለያ ተደርጎላት እስሩ በግማሽ ቀንሶላታል።
ለብሔራዊ ደኀንነት በሚል የአንቻ ክሶች ይታዩ የነበረው በዝግ ችሎት ነበር።