ስድስት አይረሴ የዶናልድ ትራምፕ አስገራሚ ፎቶዎች

ዶናልድ ትራምፕ እየመረራቸውም ቢሆን ነገ በአሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር ቀትር ላይ ከነጩ ቤተ መንግሥት ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ውልቅ ብለው መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡

አንዳንድ ፎቶዎች ውዝግብ ያልተለየውን ዘመናቸውን ያስታውሳሉ፡፡ እስኪ ስድስቱን ብቻ እንመልከት፡፡

1ኛ፡- "ለኔ በዓል የተገኘው ሕዝብ ከኦባማ ይበልጣል"

ልክ ከነገ 4 ዓመት በፊት በጥር 20፣ 20017 ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን እያከበሩ ነበር፡፡

ይህ ክብረ በዓል እንዳለቀ ነበር ትራምፕ መነጫነጭ የጀመሩት፡፡ ሐሳዊ ሚዲያ የሚሏቸውን መገናኛ ብዙኃን ጥርስ ነከሱባቸው፡፡

‹ምን አጠፋን? ቢሉ በበዓለ ሲመቴ የተገኘውን ሕዝብ አሳንሳችሁ ነው የዘገባችሁት አሉ፡፡ አውቃችሁ ሰው የሳሳበት ቦታ መርጣችሁ ፎቶ አነሳችሁ፤ ቪዲዮ ቀረጻችሁ ብለው ከሰሱ፡፡

ለኔ ቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኘው ሕዝብ ስፍር ቁጥር የለውም አሉ፡፡

ትራምፕን ያቆሰላቸው ምናልባት የሳቸው በዓል በባራክ ኦባማ በዓለ ሲመት የተገኘው ሕዝብ ብዛት ጋር ሲነጻጸር ኮሳሳ መሆኑ ነበር፡፡

የያኔው የዋይት ሐውስ ፕሬስ ኃላፊ ‹‹በአሜሪካ ታሪክ በበዓለ ሲመት ከተገኘው ሕዝብ ሁሉ የላቀው የትራምፕ ነው›› በማለት የአባይነት ዘመናቸውን ሀ ብለው ጀመሩ፡፡

2፡- ለወዳጅም ለጠላትም ያስቸገሩት ትራምፕ

ትራምፕ ከአሜሪካ ታሪካዊ ጠላቶች ብቻም ሳይሆን ከአሜሪካ ታሪካዊ ወዳጆችም ጭምር ዐይንና ናጫ በመሆን ነው ዘመናቸውን ያሳለፉት፡፡

ካላመናችሁ ይህን ፎቶ ተመልከቱ፡፡ በ2018 ሰኔ ላይ ትራምፕ በ7ቱ ብልጹግ አገራት ስብሰባ ላይ ካናዳ ተገኝተው ነበር፡፡

ስብሰባው ሊጀመር ሲል በብረትና አልሙኒያም ገቢ ንግድ ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ በካናዳ፣ አውሮጳ ኅብረትና ሜክሲኮ ላይ መጣላቸውን ትራምፕ አስታወቁ፡፡

ይህን ተከትሎ ማክሮንና ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳ ላይ መሞላለጭ ጀመሩ፡፡

ከላይ የምትመለከቱት ፎቶ አንጌላ መርከልና ሌሎች መሪዎች አልጨበጥ ባሏቸውና የልጅ ባህሪን እያሳይዋቸው በተቸገሩት ትራምፕ ላይ አፍጠው ይታያሉ፡፡ እንደው ምን ይሸለናል የሚሉ ይመስላሉ፡፡

ይህ ፎቶ በአሜሪካ ወዳጅ አገራት ትራምፕ ክስተት ሆነውባቸው ‹እረ ምን ጉድ ነው? ያሉበትን የፍጥጫ ዘመን ያሳያል፡፡

3፡-" ኬረዳሽ ነኝ! እናንተስ?" ሚላኒያ ትራምፕ

ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በ2018 የለበሱት ጃኬት መነጋገርያ ሆነ፡፡ በጃኬቱ ላይ የተጻፈው ጽሑፍ ‹‹እኔ ጭራሽ ግድ አይሰጠኝም፡፡ እናንተስ?›› የሚል ነበር፡፡ ይህን ጃኬት የለበሱት ከወላጆቻቸው ተለይተው የታገቱ ሕጻናት መጠለያን በጎበኙበት ወቅት ነበር፡፡

ስደተኛ ወላጆችን ከልጆቻቸው የመለያየት ፖሊሲን በመከተላቸው ባላቸው በሚብጠለጠሉበት ወቅት ይህን ጃኬት መልበሳቸው ምን ለማለት ፈልገው ነው በሚል ቀዳማዊት አመቤት ሜላኒያ ከፍ ዝቅ ተደርገው ነበር በጊዜው፡፡

4፡- የናንሲ ፒሎሲ የፌዝ ጭብጨባ

አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲና ትራምፕ መናቆር የጀመሩት ድሮ ነው፡፡ ይህ ፎቶ ግን ሁሉን ይናገራል፡፡

ትራምፕ በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነበር በየካቲት 2019 ይህን የሹፈት ጭብጨባ ያሳዩት፡፡

ፒሎሲ ወደው አይደለም፡፡ ትራምፕ አልጨብጥም ብለው ንቀት አሳይተዋቸዋል፡፡ አፈ ጉባኤዋ ፒሎሲ እሳቸውን አስተዋውቀው ነበር ንግግሩ መጀመር የነበረበት፤ ትራምፕ ይህን ደንብ ጥሰዋል፡፡

በትራምፕ ‹ጋጠወጥ› ባህሪ የተበሳጩት ፒሎሲ ታዲያ ይህን ዝነኛ የሆነውን የፌዝ ጭብጨባ አጨበጨቡ፡፡ አሁን በአጫጭር መልእክቶች ልውውጥ እጅግ ተወዳጁ የሹፈት ደቂቀ ምሥል (ኢሞጂ) ሆኖ ዓለም ያውቀዋል፡፡

5. የኪም ጆንና የትራምፕ ረመጥ ፍቅር

በአሜሪካ ታሪክ ባልተለመደ መልኩ ከሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ጋር የተገናኙት ትራምፕ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ሆኖም መገናኘታቸው ፍሬ አላፈራም፡፡

በምሥሉ ላይ ትራምፕና ኪም ሰሜንና ደቡብ ኮሪያን የሚለያየውን መስመር ሲራመዱ ይታያሉ፡፡ ጊዜው ሰኔ 2019 ነበር፡፡

ኪምና ትራምፕ እንዲህ በወዳጅነት መንፈስ ከመገናኘታቸው በፊት በደብዳቤ ሲሞላለጩ ነበር፡፡

6፡- ነውጥን ያራገቡት ፕሬዝዳንት

ትራምፕ ለነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው 70 ደቂቃ የረዘመ ንግግር አደረጉ፡፡ በዚህ እሳት በለኮሰ ንግግራቸው ባይደን ተሸንፏል፣ ምርጫው ተጭበርብሯል፤ ለምን ሄደን ካፒቶል ሒልን አንወረውም ብለው ሐሳብ አቀረቡ፡፡

ነውጠኛ ደጋፊዎቻቸው የትምፕን ሐሳብ ተቀብለው በጭራሽ ይደፈራል ተብሎ ያልታሰበውን ካፒቶል ሒልን ወረሩት፡፡

አምስት ሰዎች ሞቱ፡፡ ስብሰባ ላይ የነበሩት የታችኛውና የላይኛው የተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች እንዲደበቁ ተደረገ፡፡

ትራምፕም ሁለት ጊዜ በመከሰስ በአሜሪካ ታሪክ አዲስ የቅሌት ክብረ ወሰን አስመዘገቡ፡

አምስት ሰዎች ሞቱ፡፡ ስብሰባ ላይ የነበሩት የታችኛውና የላይኛው የተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች እንዲደበቁ ተደረገ፡፡

ትራምፕም ሁለት ጊዜ በመከሰስ በአሜሪካ ታሪክ አዲስ የቅሌት ክብረ ወሰን አስመዘገቡ፡