ሳዑዲ አረቢያ በሞት የምትቀጣቸው ሰዎች ቁጥር ቀነሰ

ሳዑዲ አረቢያ በሞት የምትቀጣቸው ሰዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ተገኝቷል።

የሳዑዲ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዳለው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 27 ሰዎች ብቻ ናቸው በሞት የተቀጡት።

ይህም ከ2019 (እአአ) ጋር ሲነጻጸር የ85 ከመቶ ቅነሳ አሳይቷል።

ይህ ለምን ሆነ በሚለው ዙርያ ዘገባው ምናልባት ከአደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ጥፋተኞቹ አንድ ዕድል እንዲሰጣቸው እየተደረገ በመሆኑ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ።

ሆኖም ሳዑዲ አረቢያ በ2021 በሞት የምትቀጣቸው ሰዎች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ስጋትም አብሮ ይነሳል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኑ እንዳለው ለሞት ቅጣት መቀነስ ሌላው ምክንያት የኮቪድ-19 ተህዋሲ ወረርሽኝ ነው።

ምክንያቱም መንግሥት ከጥር እስከ ሚያዝያ በእንቅስቃሴ ገደብ የተነሳ አንድም ሰው በስቅላት አልቀጣም ብሏል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደዘገበው በ2019 ሳኡዲ አረቢያ 184 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች፤ ከነዚህ ውስጥ ግማሾቹ የውጭ አገር ዜጎች ሲሆኑ ስድስቱ ሴቶች ናቸው።

ባለፈው ዓመት የሳዑዲ ንጉሥ እድሜያቸው ከ18 በታች የሆኑ አዳጊዎችን በሞት እንዳይቀጡ ከዚያ ይልቅ ወደ 10 ዓመት የእስር ቅጣት እንዲቀየርላቸው ማዘዛቸው ተዘግቦ ነበር።

ሆኖም ይህ የንጉሡ አዋጅ በጋዜጣም ሆነ በማንኛውም ሕግ ላይ የተቀመጠ ባለመሆኑ 5 ወጣት ጥፋተኞች የሞት ቅጣትን እየጠበቁ ነው ተብሏል።

ምናልባትም ቅጣቱ ተፈጻሚ ላይሆንባቸው ይችላል።

ሞት ቅጣትን በመጠባበቅ ከሚገኙት መካከል እድሜያቸው ከ15 እስከ 17 የሚሆኑ 3 የሺአ ሙስሊም ተከታይ ወጣቶች ይገኙበታል።

በሳዑዲ የሚገኙ አንዳንድ መንፈሳዊ መሪዎች ሞት የተበየነባቸው የተለየ ፖለቲካዊ አመለካከት አሳይታችኋል በሚል ሰበብ ነው ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሳኡዲን ይከሳሉ።

ለምሳሌ ሳልማን አል ኡዴህና ሐሰን ፋህራን አልማሊኪ ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ሁለት ተራማጅ መንፈሳዊ መሪዎች በ2017 የታሰሩ ሲሆን ከሌሎች ምሁራን፣ የሴቶች መብት ተሟጋቾችና ከአብአዊ መብት ተቆርቋሪ የሳዑዲ ዜጎች ጋር በመሆን ሞት ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል ስጋት አንዣቧል።

ሳዑዲ የዜጎችን መብት በመጨፍለቅና የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ዜጎቿን በሰው አገርም ቢሆን ገዳይ ቡድን በማስላክ ደብዛቸውን በማጥፋት ትታወቃለች።

ከዓመታት በፊት በቱርክ ኢስታንቡል የሳዑዲ ቆንጽላ ውስጥ ያስገደለችው ጀማል ካሾግጂ የአገዳደሉ ሁኔታ በመላው ዓለም ከፍተኛ ድንጋጤን መፍጠሩ አይዘነጋም።

ካሾግጂ የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ በተለይ በንጉሣዊያን ቤተሰብ የመብት ረገጣ ዙርያ የሰላ ትችት በመጻፍ የሚታወቀውን የሰብአዊ መብት ታጋይና ጋዜጠኛ ነበር።