ስፖርት፡ በቻን የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ላይ በዋና ዳኝነት የምትሳተፈው ሊዲያ ታፈሰ

ሊዲያ ታፈሰ

የፎቶው ባለመብት, CAF

የምስሉ መግለጫ, በካሜሮን በሚካሄደው ቻን የወንዶች እግር ኳስን ከሚዳኙ 19 ዋና ዳኞች መካከል ብቸኛዋ የመሃል ዳኛ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ሊዲያ ታፈሰ

ዛሬ ቅዳሜ ጥር 08/2013 ዓ.ም ካሜሩን ውስጥ የሚጀመረው 'ቻን' በመባል የሚታወቀው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ጨዋታዎችን እንዲዳኙ በአህጉሪቱ የእግር ኳስ የበላይ አካል ካፍ ከ31 አገራት 47 ዋና ዳኞችና ረዳት ዳኞችን ሰይሟል።

ይህን የወንዶች የእግር ኳስ ውድድር ከሚዳኙት ዳኞች መካከል አራት ሴቶች ከወንዶች አቻዎቻቸው ጋር በአካላዊና ስፖርታዊ እንዲሁም የእግር ኳስ ጨዋታን በመረዳት ባላቸው ብቃት ተመዝነው እንደተመረጡ ተገልጿል።

ለውድድሩ ዳኝነት ከተመረጡት 47 ዳኞች መካከል፣ 19ኙ በዋና ዳኝነት ጨዋታዎችን የሚመሩ ሲሆን ቀሪዎቹ በመስመር ዳኝነትና በቪዲዮ ዳኝነት የመሃል ዳኞችን የሚያግዙ ናቸው። ታዲያ ከ19ኙ ዋና ዳኞች መካከል ብቸኛዋ የመሃል ዳኛ ኢትዮጵያዊቷ ሊዲያ ታፈሰ ናት።

ሊዲያ በአገር ውስጥና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን በመዳኘት ብቃቷን ያስመሰከረች ስትሆን የአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ውስጥ አንዱ በሆነው 'የቻን' የወንዶች የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ በዋና ዳኝነት ጨዋታ የምትመራ ቀዳሚዋ ሴት ሆናለች።

ካፍ የሚያዘጋጃቸው የወንዶች የእግር ኳስ ውድድሮችን በመዳኘት በኩል ሴቶች እንዲሳተፉ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ፣ በውድድሮቹ ሂደት ውስጥ ሴቶች የተለያዩ ኃላፊነቶችን በመያዝ እንዲሳተፉ እያደረገ ነው። በዚህም መሠረት ከሊዲያ ታፈሰ በተጨማሪ በቻን ውድድር ላይ በረዳት ዳኝነት ከማላዊ፣ ከናይጄሪያና ከካሜሩን የተመረጡ ሴቶች ይሳተፋሉ።

የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ሊዲያ ታፈሰ ወደ ስፖርት የገባቸው ጅማ ውስጥ ባዳበረችው የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ፍቅር ምክንያት ነው። ሊዲያ በታዳጊነቷ እግር ኳስ ትጫወት የነበረ ሲሆን ዋነኛው ስፖርቷ ግን ቅርጫት ነበር።

አሁን በኢትዮጵያ ከፍተኛ የወንዶች እግር ኳስ ሊግ ውስጥ በብቃታቸው ከሚጠቀሱ ዳኞች መካከል አንዷ የሆነችው ሊዲያ፣ መጀመሪያ ላይ ባገኘችው ስልጠና ተስባ ነበር ወደ ዳኝነቱ የገባችው።

በዳኝነቱ ዘርፍ ከሴቶች አንጻር ከቀዳሚዎቹ ውስጥ የምትጠቀሰው ሊዲያ፣ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን መዳኘት በጀመረች ጊዜ፣ ጥያቄና ፈተናዎች ገጥመዋት እንደነበር ካፍ ድረ ገጽ ላይ በወጣው ታሪኳ ላይ ሰፍሯል።

"በጣም አስቸጋሪ ነበር። አንዳንዶች ሌላ ሴት በሌለችበት ዘርፍ ላይ በእግር ኳስ ዳኝነት ለመሰማራት ለምን እንደወሰንኩ ሁሉ የሚጠይቁኝ ሰዎች ነበሩ" ትላለች።

ሴት ዳኞችን ለማፍራት በታቀደ ፕሮጀክት ውስጥ ስልጠና አግኝታ፣ ከ15 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ልጆች የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በዳኝነት በመምራት የጀመረችው ሊዲያ፤ በአገሪቱ ፐሪሚየር ሊግ ውስጥ ጨዋታዎችን በዳኝነት መምራት ችላለች።

ሊዲያ ታፈሰ

የፎቶው ባለመብት, Lidiya Tafesse

በዳኝነቱ ላይ ያሳደረችው ፍቅር ቢጠነክርም፣ ሴት ሆና የወንዶችን ጨዋታዎች ስትዳኝ እንደ እንግዳ ነገር የሚመለከቷት ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን ከወንዶች ጋር እግር ኳስ በምትጫወትበት ጊዜ ያዳበረችው በራስ መተማመን የወንዶችን ውድድሮች ያለችግር እንደትመራ እንደረዳት የምትናገረው ሊዲያ፤ የቤተሰቧ ድጋፍ ደግሞ ወሳኙ እንደነበር ታነሳለች።

በአገር ውስጥ ውድድሮች ላይ ባሳየችው የዳኝነት ብቃት ለዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎች የታጨችው ሊዲያ፤ በመጀመሪያ ከ15 ዓመት በፊት ናይጄሪያና ላይቤሪያ አቡጃ ውስጥ ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ውድድር ለዋንጫ ለማለፍ ያደረጉትን ግጥሚያ ዳኝታለች።

"ያንን ጨዋታ አልረሳውም ምክንያቱም በጣም አስቸጋሪ ነበረ። ስታዲየሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ከምናውቀው በጣም ይተልቃል፣ ተመልካቹም የተለየ ነበር" ትላለች።

በመቀጠልም የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ግጥሚያዎችን ያጫወተች ሲሆን በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደውን የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ውድድርን በተከታታይ ለአራት ጊዜ በመዳኘት ለቀጣዩ እየተዘጋጀች ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ከአራት ዓመት በፊትና ከአንድ ዓመት በፊት የተካሄዱትን የፊፋ የሴቶች እግር ኳስ የዓለም ዋንጫን፣ እንዲሁም የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች የዓለም ዋንጫንና ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች ላይ በዳኝነት ተሳትፋለች።

ሊዲያ ልጇን በጸነሰችበትና ከወለደች በኋላም ወደምትወደው የዳኝነት ሙያዎ ለመመለስ ፈተናዎች ገጥመዋት ነበር።

"ከእርግዝና በኋላ አካላዊ ለውጥ ያጋጥማል። ክብደቴ በጣም ጨምሮ ስለነበር ወደ ቀድሞ አቋሜ ለመመለስ በጣም መስራት ነበረብኝ። በርትቼ በመስራት መጨረሻ ላይ ተሳክቶልኝ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ እድሉን አገኘሁ" ብላለች።

ለዚያ ውድድር በምትዘጋጅበት ጊዜ ጉዳት አጋጥሟት እንደነበር የምትናገረው ሊዲያ፣ ወደ አገሯ እንደምትመለስና በዚህ ምክንያት ከስፖርቱ ልትወጣ እንደሆነ ስጋት ፈጥሮባት ነበር። ነገር ግን በኋላ ላይ አገግማ ዛሬ ላይ ደርሳለች።

ከጉዳቷ በኋላ ወደ ተጨማሪ ሰዓት የተሸጋገረውን የካሜሩንና የኮትዲቯርን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ መርታ ነበር። "ጨዋታው ወደ ተጨማሪ ሰዓት ሲሸጋገር ሜዳ ውስጥ ከእግር ኳስ ተጫዋቾቹ በላይ ጠንካራ ነበርኩ። በጣም ደስ ብሎኝ ነበረ" ስትል ሊዲያ ታስታውሳለች።

ሊዲያ በበርካታ ታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ወሳኝ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ በዳኝነት ተሳትፋለች። ወደፊትም በታላቁ የአፍሪካ የወንዶች ዋንጫ ላይ በዳኝነት እንደምትሳተፍ ተስፋ አላት።

ሊዲያ ከዳኝነቱ በተጨማሪ የፋርማሲ ባለሙያ ስትሆን፣ በዚህ የኮሮናቫይረስ ዘመን የእግር ኳስ ውድድሮች ለወራት ተቋርጠው በነበረበት ጊዜ በሙያዋ ወገኖቿን ለማገልግል ሰርታለች። በዚህም ሰዎች ራሳቸውንና ሌሎችን ከወረርሽኙ እንዲከላከሉ የህክምና መረጃዎችን በተለያዩ መንዶች ስትሰጥ ቆይታለች።

በየትኛውም ጊዜ ከልምምድ ርቃ የማታውቀው ሊዲያ፣ እንደ ሴት በቤተሰቧና በእግር ኳስ ዳኝነት ሙያዋ መካከል ያለውን ሚዛን በመጠበቅ እንደተሳካላት ትናገራለች። ለዚህ ደግሞ ከባሏና ከልጇ የምታገኘው ድጋፍና ማበረታታት በሙያዋ በስኬት እንደትቀጥል እንዳደረጋት ገልጻለች።

በአፍሪካ አህጉር አሉ ከሚባሉ ኮከብ ሴት የእግር ኳስ ዳኞች መካከል ከፊት የምትጠቀሰው ሊዲያ ታፈሰ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ውስጥ ወደፊት ለሚመጡ ሴት ዳኞች መልካም አርአያ እንደምትሆን ታምናለች።

ወደፊትም ከሙሉ ጊዜ የእግር ኳስ ዳኝነት አረፍ ስትል በፋርማሲ ሙያዋ ከመቀጠል በተጨማሪ፣ በዳኝነቱ የእሷን እግር ተከትለው መሥራት የሚፈልጉትን የማሰልጠን ፍላጎት አላት።