ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጥቁር አሜሪካዊውን በ7 ጥይት የመታው ነጭ ፖሊስ 'ክስ አይመሰረትበትም'
በዊስኮንሲን ግዛት፣ ኬኖሻ ከተማ ውስጥ ፖሊስ ሦስት ልጆቹ ፊት በጥይት ደብድቦት በተአምር የተረፈው ጄኮብ ብሌክ በጠበቃው በኩል የፍትሕ ያለህ እያለ ነው።
የአካባቢው ዐቃቤ ሕግ ድርጊቱን በፈጸመው ፖሊስ ላይ የወንጀል ክስ አይመሰረትም ማለቱን ተከትሎ የጄኮብ ጠበቃ አሜሪካ ሦስት የፍትሕ ሥርዓት ነው ያላት ሲሉ ለሚዲያ ተናግረዋል። አንዱ ለነጭ ፖሊሶች፣ ሌላው ለተራው ሕዝብ እና የመጨረሸው ደግሞ ለጥቁሮች ነው ሲሉ ቁጣቸውን ገልጠዋል።
ጄኮብ ደጅ ቆማ ወደነበረችው መኪናው ሲራመድ ሁለት ፖሊሶች በቅርብ ርቀት እየተከተሉት ነበር። የመኪናውን በር እንደከፈተ ግን 3 ሕጻናት ልጆቹ ከኋላ ወንበር ተቀምጠው ድርጊቱን እየተመለከቱ 7 ጥይቶች ከጀርባው ሲተኮሱበት ይታያል።
ይህ በተንቀሳቃሽ ምሥል ዓለም የተመለከተው ቪዲዮ እያለ እስከአሁን በጉዳዩ ተጠያቂ የሚሆን አንድም ፖሊስ እንዳልተከሰሰ ተዘግቧል። ወደፊትም በወንጀል የሚጠየቅ የፖሊስ መኮንንም አይኖርም ተብሏል።
የጄኮብ ጠበቃ ውሳኔውን ተከትሎ እንደተናገሩት፣ ዘረኛ በሆነው የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የ20 ሰከንድ ግልጽ የቪዲዮ ማስረጃን ውድቅ ለማድረግ ዐቃቢ ሕግ 4 ወራት ፈጅቶበታል ብለዋል። "ፍትሕ ቢኖር፤ ዓይናችን ለተመለከተው ነገር የሁለት ሰዓት ማብራሪያ አስፈላጊ አልነበረም" ሲሉም ተናግረዋል።
ጥቁር አሜሪካዊው ጄኮብ ብሌክ 7 ጥይት በቅርብ ርቀት ተርፈከፍክፎበት በሕይወት ቢተርፍም ከወገብ በታች ሙሉ በሙሉ መንቀሳቀስ አይችልም።
ጄኮብ ብሌክ ከኋላው በተደጋጋሚ በፖሊስ የተተኮሰበት ወደ መኪናው እያመራ በነበረ ቅጽበት የመኪናው በር እንደከፈተ ነበር።
ይህ ሁሉ ሲሆን መኪናው ውስጥ ኋላ ወንበር ተቀምጠው የነበሩ ሦስት ሕጻናት ልጆቹ ድርጊቱን ተመልክተዋል።
በጥቁር አሜሪካዊው ጄኮብ ብሌክ ላይ ነጭ ፖሊሶች ያደረሱት ጥቃት በዊስኮንሲንና በሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀስ ይታወሳል።
ድርጊቱን በነሐሴ 23/2020 (እአአ) የፈጸመው ፖሊስ ረስተን ሼስኪይ ይባላል። እስከአሁንም የወንጀል ክስ አልተመሰረተበትም።
ይህን ድርጊት ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ሁለት ሰዎች ተገድለው አንድ ሌላ ሰው በኬኖሻ ከተማ መቁሰሉ አይዘነጋም።
ፖሊስ እንዴት ላይከሰስ ቻለ?
የኬኖሻ ከተማ ዐቃቤ ሕግ ማይክል ግራቭሊ ድርጊቱን በፈጸመው የፖሊስ መኮንን ላይ እንድም የወንጀል ክስ አልተከፈተም፣ አይከፈትምም ብለዋል።
የፖሊስ መኮንኑ ሼስኪ በጄኮብ ላይ በቅርብ ርቀት ጥይት አከታትሎ ሲተኩስበት አንድ መንገደኛ ነው ቅጽበቱን በቪዲዯ አስቀርቶ በመላው አሜሪካ ቁጣ እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆነው።
ድርጊቱ የተፈጸመበት ክፍለ ከተማ ዐቃቤ ሕግ እንደሚሉት ክሱን መመሥረት አስፈላጊ የማይሆነው ፖሊስ መኮንኑ ድርጊቱን የፈጸምኩት ራሴን ለመከላከል ነው የሚለውን የክርክር ነጥብ መምዘዙ አይቀሬ ስለሚሆን ነው።
የኬኖሻ የፖሊስ መኮንኖች ማኅበር እንደሚለው ጄኮብ በጊዜው ቢላ ይዞ የነበረ ሲሆን ያን እንዲጥል በፖሊስ መኮንኑ በሚስተር ሼስኪ በተደጋጋሚ ቢነገረውም ሊሰማ አልቻለም።
የፖሊስ መኮንኑ ጠበቃ ብሬንዳን ማቲው እንዳሉት ደግሞ ጄኮብ ስለት ያለው መሳሪያ ይዞ ወደተኮሰበት ፖሊስ ዞሮ ጥቃት ለመፈጸም አስቦ ነበር።
መርማሪዎች በበኩላቸው እንደሚሉት ፖሊሱ በመኪናው ወለል ላይ ስለት ያለው ነገር እንደተመለከተ ብቻ ጠቅሰዋል፣ ጄኮብ ብሌክ ስለቱን ለመጠቀም ሙከራ ስለማድረጉ ያሉት ነገር የለም።
ቅጽበቱን የቀረጸው መንገደኛ በበኩሉ ለሲኤንኤን ቴሌቪዥን ሲናገር መቅረጽ ከመጀመሩ በፊት ፖሊስ ከጄኮብ ጋር ሲታገል፣ በጡጫ ሲመታውና በጨረር ማደንዘዣ መሳሪያ ሊያጠቃው ሲሞክር ነበር። እሱ ቪዲዮ መቅረጽ የጀመረው ከዚህ በኋላ ነበር።
20 ሰከንዶች በሚረዝመው በዚህ ቪዲዮ ላይ ጄኮብ ወደ ግል መኪናው ተራምዶ የፊት በሩን ሲከፍት በቅርብ ርቀት ደግሞ 2 ፖሊሶች ሲከተሉት ከዚያ ደግሞ የመኪናው በር እንደከፈተ አንድ ፖሊስ ከኋላው ጥይት ሲተኩስበት ይታያል።
ቅጽበቱን የቀረጸው ሰው ፖሊስ ከመተኮሱ በፊት ቢላውን ጣለው እያለ መጮኹን መስማቱን ነገር ግን ቢላ አለማየቱን አስታውሷል።
የአቃቤ ሕግ ውሳኔን ተከትሎ ቁጣ ይቀሰቀሳል በሚል በዊስኮንሲን ኬኖሻ 500 ተጨማሪ ፖሊሶች በተጠንቀቅ ተሰማርተዋል።