ሮይተርስ የካሜራ ባለሙያው አዲስ አበባ ውስጥ መታሰሩን ተቃወመ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሮይተርስ ዜና ወኪል የካሜራ ባለሙያ፣ ኩመራ ገመቹ፣ አዲስ አበባ ከሚገኘው የመኖሪያ ቤቱ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ባለቤቱ ሃዊ ደሳለኝ ለቢቢሲ ገለፀች።
ባለቤቱ ለቢቢሲ እንዳለችው ኩመራ በቁጥጥር ሥር የዋለው ባለፈው ሐሙስ፣ ታኅሣስ 15/2013 ዓ.ም ሲሆን በምን ምክንያት በፖሊስ በቁጥጥር ስር ሊውል እንደቻለ ምታውቀው ነገር እንደሌለ ገልጻለች።
ኩመራ የሚሰራበት ዓለም አቀፉ የዜና ወኪል ሮይርስም የእስሩን ምክንኣት ለማወቅ ለፖሊስ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን ገልጿል።
ሮይተርስ ቤተሰቦቹን ጠቅሶ እንደዘገበው እስካሁን ድረስ ኩመራ ላይ ክስ አልተመሰረተበትም።
ቢቢሲ ጠቅላይ አቃቤ ሕግን ስለ ኩመራ መታሰር መረጃ ለማግኘት ሙከራ ቢያደርግም ጉዳዩን እያጣሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኩመራ ገመቹ ለሮይተርስ የዜና ወኪል በካሜራ ባለሙያነት ለረዥም ዓመታት እያገለገለ ይገኛል።
ኩመራ አርብ ታህሣስ 16/2013 ዓ.ም ያለ ጠበቃ ፍርድ ቤት መቅረቡ የተገለፀ ሲሆን ፖሊስ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀን በመጠየቁ ችሎቱ እንደፈቀደለት ባለቤቱ ለቢቢሲ አረጋግጣለች።
ሰኞ ታህሣስ 19/2013 ዓ.ም ሮይተርስ ባወጣው መግለጫ የኩመራን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋል አውግዟል።
የካሜራ ባለሙያው በቁጥጥር ሥር የዋለውም ታህሣስ 7/2013 ዓ.ም የድርጅቱን የፎቶግራፍ ባለሙያ ሁለት ፖሊሶች ከደበደቡ በኋላ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።
"ኩመራ በኢትዮጵያ ፍትሃዊ፣ ገለልተኛ እና ነጻ የሆነ ዘገባ የሚሰራው የሮይተርስ ዜና ወኪል ቡድን አባል ነው። የኩመራ ሥራ ገለልተኛ መሆኑን እና ሙያውን የጠበቀ መሆኑን ማሳያ ነው። እንዲሁም ለመታሰሩ ምንም መሰረት እንደሌለ ተረድተናል" ሲል የሮይተርስ ዜና ወኪል ከፍተኛ አርታኢ ስቴፈን ጄ አድለር በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
"ጋዜጠኞች ያለ አንዳች ፍርሃት ወይንም ጉዳት በየትኛውም ሥፍራ ሆነው መዘገብ አለባቸው፤ ኩመራ ነጻ እስኪሆን ድረስ አናርፍም" ብለዋል አድለር በመግለጫቸው ላይ።
ሐሙስ ዕለት ማታ በቁጥር አስር የሚሆኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት አዲስ አበባ በሚገኘው የኩመራ ቤት በመገኘት በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉት ባለቤቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የሦስት ልጆች አባት የሆነው ኩመራ በቁጥጥር ሥር ሲውል በልጆቹ ፊት መሆኑን የምትናገረው ባለቤቱ፣ ፖሊሶች እጁን ወደ ኋላ በካቴና አስረው ወስደውታል ስትል ለቢቢሲ የነበረውን ሁኔታ አስረድታለች።
ከዚያ ዕለት ጀምሮ ልጆቹ ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውንና መተኛት እንደተቸገሩም አክላ ገልጻለች።
እንደ ቤተሰቡ ገለፃ ከሆነ ፖሊስ የኩመራን ስልክ፣ ኮምፒውተር፣ ፍላሽ ድራይቭ እንዲሁም ወረቀቶችን ወስዷል።
ቢቢሲ ኩመራ በአሁኑ ሰዓት ታስሮ የሚገኘው ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ እስር ቤት ውስጥ በአንድ ቀዝቃዛ ክፍል ብቻውን መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዲቀላቀል ቢጠይቅም መከልከሉን ለማወቅ ችሏል።
መንግሥት በትግራይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ፣ በውጭ አገር መገናኛ ብዙሃን ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ሲያሳድር እንደነበር የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል።
ሮይተርስ ኩመራ የትግራይ ግጭትን መዘገቡን ገልጾ፣ ለኢትዮጵያ የመንግሥት ባለሥልጣናት የታሰረው በዚህ ምክንያት መሆን አለመሆኑን ቢጠይቅም ምላሽ አለማግኘቱን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሮይተርስንና ሌሎች የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን በኅዳር 14/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ "ሐሰተኛ" እና "ሚዛናዊ የሆነ ዘገባ ባለማቅረብ" ከስሶ ነበር።
ሮይተርስ በወቅቱ በትግራይ እና በፌደራል መንግሥቱ ግጭት ላይ በሰራው ዘገባ ላይ የቀረበውን ክስ ተቃውሞ መግለጫ አውጥቷል።
መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ በበኩሉ የኩመራ እስር በአገሪቱ እየታየ ያለው የፕሬስ ነጻነት ጥሰት ማሳያ መሆኑን ገልጿል።
ሲፒጄ ኅዳር 22/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ሰባት ጋዜጠኞች በሰሯቸው ዘገባዎች ምክንያት እስር ቤት መግባታቸውን ገልጾ ነበር።
ከእነዚህ መካከል አምስቱ የታሰሩት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት ኃይሎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው።












