እስራኤል በሁለት ዓመት ውስጥ ለ4ኛ ጊዜ ምርጫ ልታደርግ ነው

እስራኤል በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ ምርጫ ለማድረግ ልትገደድ ነው።

እስራኤል ወደ ምርጫ ለመግባት የተገደደችው በስልጣን ላይ ያለው የጥምር መንግሥት በአገራዊ በጀት ጉዳይ ሊስማማ ባለመቻሉ ነው።

እስራኤል ባለፉት ጊዜያት ያካሄደቻቸው ምርጫዎች አሸናፊውን ፓርቲ በማያሻማ ሁኔታ ነጥለው የሚለዩ አልሆኑም።

የሙስና ክስ ያለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለ6ኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመናቸውን መቀጠል ይሻሉ።

ኔታንያሁ "የተመሰረተብኝ ክስ ሐሰተኛና ፖለቲካዊ አሻጥር ያለው ነው" ሲሉ ያስተባብላሉ።

እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመምራት እንደሳቸው ረዥም ዘመን በትረ ሥልጣን ይዞ የቆየ የለም።

ማክሰኞ እኩለ ሌሊት ላይ የእስራኤል ፓርላማ ተበትኗል።

ይህም የሆነው የ2021 አገራዊ በጀት ላይ ፓርቲዎች መስማማት ባለመቻላቸው ሲሆን፤ የአገሪቱ ሕግ ያ በሚያስገድደው መሰረት ፓርላማው ለመበተን ተገዷል።

ፓርላማው እንዳይበተን ለማድረግ ባለቀ ሰዓት ውይይቶች ቢደረጉም አልተሳኩም።

የእኩለ ሌሊቱ የሰዓት ገደብ ማለፉን ተከትሎ የሊኩድ ፓርቲ መሪ ቤንያሚን ኔታንያሁና ተቀናቃኛቸው የብሉ ኤንድዋይት ፓርቲ ቤኒ ጋንዝ እስር በእርስ ተወነጃጅለዋል።

“እኔ ይህን ምርጫ አልፈኩትም፤ ሊኩድ ፓርቲዬ ይሄን ምርጫ አይፈልገውም። በተደጋጋሚ ምርጫ ውስጥ እንዳንገባ ብዙ ጥረናል። ነገር ግን ቤኒ ጋንዝ ሊተባበር አልቻለም” ሲሉ ወቅሰዋል፣ ኔታንያሁ።

ኔታንያሁ ጨምረውም "ሊኩድ ፓርቲ በመጪው መጋቢት 23 የሚደረገውን ምርጫ በሰፊ ልዩነት እንደሚያሸንፍ አልጠራጠርም" ብለዋል።

ቤኒ ጋንዝ በበኩላቸው የኔታናያሁ ንግግር "በውሸት የታጨቀ ነው" ብለዋል።

"ኔታንያሁ ምርጫው እንዲካሄድ ይፈልጋል፤ ምክንያቱ ደግሞ የሙስና ክሱን ለመጋረድ ነው" ብለዋል።

ኔታንያሁና ቤኒ ጋንዝ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የጥምረት መንግሥት መሥርተው አብረው ሲሰሩ ነበር። ስምምነታቸውም በፈረቃ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ነበር።

በዚህም መሰረት ኔታንያሁ እስከ 2021 ኅዳር ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከቀጠሉ በኋላ ቤኒ ጋንዝ ይከተላሉ።

አሁን ይህ ጥምረት በመፍረሱ ነው በ2 ዓመት ውስጥ ለ4ኛ ጊዜ በአገሪቱ ምርጫ ሊደረግ ቀን የተቆጠረው።

የሕዝብ አስተያየት ዳሰሳዎች የቤኒ ጋንዝ ፓርቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድጋፉን እያጣ እንደሆነ የሚጠቁሙ ናቸው። ይህም የሊኩድ ፓርቲ በቀጣዩ ምርጫ አብላጫ መቀመጫን ያሸንፍ ይሆናል የሚል መላምት እንዲሰጥ አድርጓል።

በአንጻሩ በሙስና ክስ የተነሳ ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ የገቡት ኔትንያሁ በየሳምንቱ የተቃውሞ ሰልፍ የሚወጣባቸውመሪ ሆነዋል። ተቃውሞዎቹ እየተደረጉባቸው ያለው በዋናነት በአገሪቱ የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር በበቂ አልሰሩም በሚል ነው።

ኔታንያሁ የሙስና ክሳቸው በየካቲት ወር ላይ ይንቀሳቀሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኔታንያሁ ከቤኒ ጋንዝ ሌላ በቅርቡ ከሊኩድ ፓርቲ ተነጥለው አዲስ ቀኝ ዘመም ፓርቲ ከመሰረቱት ጌዲዮን ሳር ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።