ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ፈጣሪ ይቅር ሊለኝም ላይለኝም ይችላል” ሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪው
ሻፊላህ አፍጋኒስታናዊ ነው። በ16 ዓመቱ ወደ ቱርክ እየሄደ መሆኑን ለቤተሰቦቹ በስልክ አስታውቆ ነበር።
ያኔ ከሱ ጋር ድንበር የሚያቋርጡ 100 ሰዎች ነበሩ።
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ልክ እንደሱው ወደ አውሮፓ ይሰደዳሉ።
ወደ ኢስታንቡል እንዲወስዱት የከፈላቸው ሰው አዘዋዋሪዎች ፖሊሶች እንዳይዟቸው ቫን በተባለ ሀይቅ ምሽት ላይ ለመጓዝ ወሰኑ።
በምሽት እየተጓዙ ሳለ ጀልባቸው ሰጠመ። 32 አፍጋኒስታናውያን፣ ሰባት ፓኪስታናውጣን እና አንድ ኢራናዊ ጭኖ ነበር።
ከአደጋው በኋላ የ61 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል። ሻፊላህን ጨምሮ የት እንደደረሱ ያልታወቁ ስደተኞችም አሉ።
ስደተኞቹን ያጓጓዘው ካቡል ውስጥ ያለ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪ ነው። ቢቢሲ ይህንን ግለሰብ አነጋግሮት ነበር።
“የሰው ዝውውር ለብቻ የሚሠራ አይደለም”
ኤልሀም ኑር (ስሙ ተቀይሯል) ስደተኞችን ወደ ፈረንሳይ፣ ጣልያን እና ዩናይትድ ኪንግደም በመላክ ይታወቃል።
አብረውት የሚሠሩ ሰዎች ብዙ ናቸው።
“የሰው ዝውውር ለብቻ የሚሠራ አይደለም። ሁላችንም አዘዋዋሪዎች ትስስር አለን” ይላል።
ብዙ አፍጋኒስታንን ጥለው የሚወጡ ደንበኞች አሉት።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ አሁን ላይ ከአፍጋኒስታን የወጡ ዜጎች 2.7 ይሆናሉ። በከፍተኛ ሁኔታ ሰው ከሚሰደድባቸው ሶርያ እና ቬንዝዌላ ቀጥሎ ያለችው አገር አፍጋኒስታን ናት።
ስለዚህም ኤልሀም ሁሌም የሚያጓጉዘው ሰው አያጣም።
ብዙ አፍጋኖች ከአገራቸው የሚወጡት እንደ ኤልሀም ባሉ አዘዋዋሪዎች አማካይነት ነው።
ወደ አውሮፓ ለመድረስ ወጥነው ከአገራቸው ከሚወጡት የሚሳካላቸው ጥቂቱ ናቸው።
የሻፊላህ አጎት አሸር አፍዘል ጉዞው ከባድ እንደሆነ ያውቃሉ። ሆኖም ግን ሻፊላህ ደብዛው ይጠፋል ብለው አልጠበቁም።
ቤተሰቡ ሻፊላህ የት እንደደረሰ አለማወቁ ሀዘኑን አብሶባቸዋል። አስክሬናቸው የተገኘ ስደተኞች ቀብር ተፈጽሟል። ለሻፊላህ ግን ምንም ማድረግ አልተቻለም።
“ይኖራል ብለን አንጠብቅም። አስክሬኑን ብናገኝ ነው የምንለው” ይላሉ አጎቱ።
ሻፊላህ 1,000 ዶላር ለኤልሀም ከፍሎ ነበር ከአገር የወጣው። ከሌሎች ስደተኞች ጋር በእግርም በጭነት መኪናምተጉዘው በኢራን አልፈው ቱርክ ደርሰው ነበር። ሆኖም ቫን ሀይቅ ላይ ህልማቸው ተቀጨ።
ኤልሀም ከሻፊላህ ተቀብሎ የነበረውን ገንዘብ ለቤተሰቡ እንደመለሰ ይናገራል።
“እስከ ጣልያን ለመሄድ 8,500 ዶላር ይከፈላል”
ከአፍጋኒስታን ቱርክ 1,000 ዶላር፣ ከቱርክ ወደ ሰርቢያ 4,000 ዶላር፣ ከሰርቢያ እስከ ጣልያን 3,500 ዶላር ያስከፍላሉ። ባጠቃላይ 8,500 ዶላር ማለት ነው።
ኤልሀም በእያንዳንዱ ስደተኛ ከ3,000 እስከ 3,500 ዶላር ያገኛል።
የማያውቃቸውን ወይም እሱን ከሚያውቁ ሰዎች ጋር የማይተዋወቁ ሰዎችን አያገኝም።
ሰነድ ለሌላው ስደተኞች ጉዞው ከባድ እንደሆነ ያውቃል። ቀን ተደብቀው ማታ ማታ ብቻ ነው የሚጓጓዙት።
በቴህራን፣ ቫን እና ኢስታንቡል ስደተኞቹ ስውር ቤቶች እንዲያርፉ ይደረጋል።
ስደተኞቹ በሌቦች ኢላማ እንዳይደረጉ ሲባል ጌጣጌጥ፣ የእጅ ሰዓትና ሌላ ውድ ቁሳቁስ አይዙም። ከ100 ዶላር በላይ እንዳይዙ ኤልሀም ይመክራቸዋል።
ቱርክ ለመድረስ አንድ ሳምንት እና ከዛም በላይ ሊወስድ ይችላል።
ብዙውን ጊዜ ስደተኞች የሚመርጡት በቱርክ ወደ ግሪክ የሚወስደውን መንገድ ነው።
የአውሮፓ ድንበር ኤጀንሲ በዚህ ዓመት በአስር ወር ውስጥ 17,000 ሰዎች ወደ አውሮፓ እንደተሻገሩ ይገምታል።
ከስደተኞቹ አንዱ ሻህ እንደሚለው ከግሪክ ወደ ቦስንያ መጓዝ ከባድ ነበር። በተደጋጋሚ ወደ አገሩ እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ በስተመጨረሻ ድንበር መሻገር ችሏል።
“ድንበር ለመሻገር ስሞክር ፖሊሶች ደብድበውኛል። ብዙ እንግልት ደርሶብኛል” ይላል።
ሻህ ጣልያን ስለመድረሱ እርግጠኛ አይደለም። ግን አፍጋኒስታን ወዳሉ ስደተኛ አዘዋዋሪዎች መደወል አይፈልግም። ብዙም እርዳታ እንደማይሰጡ ይናገራል።
“ልትሞት፣ ልትታፈን፣ ልትጎዳ ትችላለህ። ማንም አይረዳህም። ሰው አዘዋዋሪዎች ፖሊሶችን ስለሚፈሩ ሊረዱህአ ይችሉም” ይላል ሻህ።
በቂ ምግብና ውሃ የለም። በረሀብና ጥም ምክንያት ሰዎች ሲሞቱም አይቷል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንደሚለው፤ ዘንድሮ ሜድትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ 1,000 ሰዎችሞተዋል።
በርካታ ስደተኞች አንድ ላይ በጀልባ ተጭነው ሲሄዱ አደጋ ይገጥማቸዋል። ሕይወታቸውንም ያጣሉ።
ከስደተኛነት ወደ ሰው ዝውውር
ኤልሀም በአንድ ወቅት ስደተኛ ነበር። አባቱ የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለ 5,000 ዶላር ለሰው አዘዋዋሪዎች ከፍለው ከአገር አስወጥተውታል።
“ጉዞዬ ከባድ ነበር። በተለይ ቡልጋርያ ባቡር ውስጥ ተደብቀን ነበር። ከባቡር እንድዘል ተገድጄም ነበር” ይላል።
ወደ ሰው ዝውውር የገባው 90 ዶላር እየተከፈለው ነበር። ዩኬ ከደረሰ በኋላም ከሰው አዘዋዋሪዎች ጋር መስራቱን ቀጥሏል።
21 ዓመቱ ላይ ፖሊሶች እያፈላለጉት እንደሆነ ሲሰማ ወደ አፍጋኒስታን ተመለሰ።
አውሮፓ የደረሱ ስደተኞች ስለሱ ስለሚያወሩ ደንበኞቹ ተበራክተው ነበር።
“ሰዎች ከአገር እንደማስወጣቸው ያምኑብኛል” ይላል።
አሁን ላይ በሱ አማካይነት 100 ሰዎች ወደ አውሮፓ እየተጓዙ ነው። ሻፊላህ የደረሰበት ጉዳት እጅግ ስላዛነው ከዚህ በኋላ ዝውውሩን እንደሚተወው ይናገራል።
“ቤተሰቦቻቸውን ደጋግሜ ይቅርታ ጠይቄያለሁ። ጉዞው ላይ ብዙ ነገር ሊገጥማቸው እንደሚችል አስቀድሜ ነግሬያቸዋለሁ። ፈጣሪ ይቅር ሊለኝም ላይለኝም ይችላል” ሲል የተሰማውን ተናግሯል።
እሱ ሰው ማዘዋወር ቢያቆምም ባያቆምም ሂደቱ መቀጠሉ አይቀርም። በሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ድንበር ማቋረጣቸው ይቀጥላል።