ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ ፡ የጦር መሳሪያ ለማስረከብ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ተጠናቀቀ
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ነዋሪው የጦር መሳሪያዎችን እንዲያስረክብ ባለፈው ሳምንት ያሰቀመጠው የጊዜ ገደብ ተጠናቋል።
አስተዳደሩ እንዳለው በሕጋዊም ሆነ በሕገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ነዋሪዎች እስከ ትናንት ማክሰኞ ታኅሳስ 6/2013 ዓ.ም ድረስ መሳሪያቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የጸጥታ አካላት እንዲያስረክቡ መታዘዙን ባለፈው ሰኞ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጦር መሳሪያዎችን ለማስረከብ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በኋላ የቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች እንደሚሰበሰቡ ጊዜያዊው አስተዳዳሪው የተገለጹ ሲሆን፤ በፍተሻው ትጥቅ የሚገኝባቸው ግለሰቦች "በሕግ ተጠያቂ ይሆናል" ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገው የጦር መሳሪያዎችን መሰብሰብ ሂደት ውስጥ በርካታ የጦር መሳሪያዎች መሰብሰባቸውን ሙሉ (ዶ/ር) ለኢቲቪ ትናንት የተናገሩ ሲሆን መጠኑም በሁሉም አካባቢ የተገኘው የጦር መሳሪያ መረጃ ተጣናቆ ሲያበቃ የሚታወቅ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው ጨምረውም እንደምሳሌ ከመቀለ ከተማ በቅርብ እርቀት በሚገኝ አራጎር በተባለ ቦታ የሚገኙ ነዋሪዎች ከ400 በላይ ጠመንጃዎችን ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ የሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥራው አንድ አካል እንደሆነ በተነገረው በዚህ የጦር መሳሪያዎችን መሰብሰብ ሂደት ጎን ለጎን የክልሉ ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የፌደሬሽን ምክር ቤት የክልሉ አስተዳደር እንዲፈርስ ከወሰነ በኋላ የተሰየመው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሥራው ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) እንደተናገሩት በክልሉ በነበረው ግጭት ምክንያት ከአንድ ወር በላይ ሥራ አቁመው የነበሩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ መደረጉን አመልክተዋል።
በዚህም መሰረት ለሳምንታት ሥራ አቁመው የነበሩ የክልሉ መንግሥት ሠራተኞች ሰኞ ታህሳስ 05/2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቦ ሥራ እንዲጀመር መደረጉን ገልጸዋል።
ከአንድ ወር በላይ በክልሉ ተቋርጦ በነበረው የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አገልግሎት ዋና ከተማዋን መቀለን ጨምሮ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ መጀመራቸው የታወቀ ሲሆን ባንኮች ሥራ ባለመጀመራቸው ነዋሪዎች እንደተቸገሩ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህንንም በተመለከተ ጊዜያዊው አስተዳዳሪ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) እንደተናገሩት የባንክ አገልግሎቶች በቅርቡ እንዲጀመር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ክልሉን ያስተዳድር በነበረው ህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ለወራት ከዘለቀ በኋላ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ በክልሉ ልዩ ኃይል ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ለሳምንታት የዘለቀ ወታደራዊ ግጭት መካሄዱ ይታወሳል።
በዚህም ወቅት የስልክ፣ የመብራትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ለሳምንታት ተቋርጠው የቆዩ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ መቆጣጠሩን ተከትሎ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።