አሜሪካ ፡ የትራምፕ ሥልጣን ሊያበቃ በተቃረበበት ጊዜ ሁለተኛው የሞት ቅጣት ተግባራዊ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, CBS
ከ20 ዓመታት በፊት አሜሪካ ውስጥ ታዳጊ ልጁን በመግደል ወንጀል ሞት የተፈረደበት አልፈርድ ቦርጊዎስ ቅጣቱ ተግባራዊ ሆኖበታል።
በዚህም በአገሪቱ ውስጥ ከሌላው ጊዜ በተለየ ባለፉት ሁለት ቀናት የሞት ቅጣት የተግባራዊ የሆነበት ሁለተኛው ሰው ሆኗል።
ከአልፈርድ በፊት ባለፈው ሐሙስ ብራንደን በርናንድ በሞት ተቀጥቷል።
የዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ጥር 20 ከመገባደዱ በፊት ሦስት ተጨማሪ ሰዎች የሞት ቅጣት እንደሚፈጸምባቸው ተገልጿል።
የሞት ቅጣት ላለፉት 17 ዓመታት ተቋርጦ ነበር። በዚህ ዓመት መባቻ ላይ ግን ቅጣቱ በድጋሚ እንዲጀመር ትራምፕ አዘዋል።
የሞት ቅጣት በተወሰነባቸው ሰዎች ላይ በአጠቃላይ ከተተገበረ፤ ከሌሎቹ በተለየ ትራምፕ ፕሬዘዳንት ብዙ ሰው በሞት የቀጡ መሪ ይሆናሉ።
ላለፉት 130 ዓመታት የአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች ሥልጣን ሊለቁ ሲሉ የሞት ቅጣትን ይገታሉ። ቀጣዩ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ጥር 20 በዓለ ሲመታቸው ይከናወናል።
ባይደን የዳልዌር ሴናተሩ ሳሉ ጀምሮም ለአስርት ዓመታት የሞት ቅጣትን እንደሚቃወሙ ሲገልጹ ነበር። ሥልጣን ከያዙ የሞት ቅጣትን እንደሚያስወግዱም አስታውቀዋል።
ፍርድ ቤት እንዳለው የሞት ቅጣት የተፈጸመበት አልፈርድ የሁለት ዓመት ሴት ልጁ ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰ ተነሯል።
የጭነት መኪና አሽከርካሪ ሳለ በቴክሳስ በኩል ሲያልፍ ልጁን እንደገደላትም ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
ዐቃቤ ሕግ እንዳለው፤ መኪናውን እያቆመ ሳለ ልጁ መኪናው ውስጥ ፈሳሽ ሲደፋባት ከመኪናው መስታወትና ከውስጠኛው ክፍል ጠርዝ ጋር አጋጭቶ ነበር የገደላት።
የአልፈርድ ጠበቆች እንዳሉት፤ አልፈርድ የአእምሮ ውስንነት (ኢንተለክችዋል ዲስኤቢሊቲ) ስላለበት በሞት ሊቀጣ አይገባም ነበር።
ሌሎች የሞት ቅጣት የተላለፈባቸው ታራሚዎች
ሊሳ ሞንተግመሪ፡ እአአ 2004 ላይ ሚዙሪ ውስጥ ነፍሰ ጡር ሴትን አንቃ ልጇን ከማህጸኗ ወስዳ አፍናለች። ጥር 12 የሞት ቅጣት ይፈጸምባታል ተብሏል። ጠበቃዋ እንደሚሉት ሊሳ ልጅ ሳለች በደረሰባት ድብደባ ምክንያት ከፍተኛ የአእምሮ ህመም አለባት። ከ1953 ወዲህ በሞት የተቀጣት የመጀመሪያዋ ሴት ትሆናለች።
ኮሪ ጆንሰን፡ ሪችመንድ፣ ቨርጂንያ ውስጥ ከነበረ አደንዛዥ እጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ በሰባት ሰዎች ግድያ ነው የተከሰሰው። ልጅ ሳለ በደረሰበት አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ሳቢያ የአእምሮ ውስንነት እንዳለበት ጠበቆቹ ተናግረዋል።
ደስቲን ጆን ሂግስ፡ እአአ 1996 ላይ ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ሦስት ወጣት ሴቶችን አፍኖ በመግደል ነው የተከሰሰው። ግለሰቡ ሴቶቹ እንዲገደሉ ዊሊስ ሀይንስ የተባለ ግብረ አበሩን አዟል እንጂ ግድያውን አልፈጸመም። ጥር 15 የሞት ቅጣት ይፈጸምበታል ተብሏል።












