ትራምፕ በመጨረሻ የሥልጣን ዘመናቸው የሞት ቅጣት እንዲተገበር ወሰኑ

ብራንደን በርናርድ

የፎቶው ባለመብት, COURTESY BERNARD DEFENSE TEAM

የምስሉ መግለጫ, ብራንደን በርናርድ

የሞት ቅጣት የተበየነበት ብራንደን በርናርድ የተሰኘው ግለሰብ ያቀረበው ይግባኝ ተሽሮ በሞት ተቀጥቷል።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሟቹን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ የሞት ቅጣት የተበየነበት ግለሰብ ግድያ እንዲፈፀም አዟል።

የ40 ዓመቱ በርናርድ በፈረንጆቹ 1999 ገና ታዳጊ ሳለ በፈፀመው ግድያ ተከሶ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው የሞት የተፈረደበት።

ግለሰቡ በ70 ዓመታት የአሜሪካ የሞት ቅጣት ታሪክ በዕድሜ ትንሹ የሞት ቅጣት ሰለባ ሆኗል።

በርናርድ የገደላቸውን ባልና ሚስት ቤተሰቦች በመርፌ ተወግቶ ከመሞቱ በፊት ይቅርታ ጠይቋል።

ትራምፕ ከሥልጣን ከመወርዳቸው በፊት ሌሎች አራት ግለሰቦች በሞት ቅጣት ይቀጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ከሆነ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ በሥልጣን ላይ እያሉ ብዙ ሰዎች በሞት ያስቀጡ ፕሬዝደንት ይሆናሉ።

የሞት ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ያሉት አራት ሰዎች ቅጣታቸው ከፀና ከሐምሌ ጀምሮ 13 ሰዎች ተቀጪዎች ይሆናሉ ማለት ነው።

አሜሪካ በታሪኳ ፕሬዝደንቶች ሲቀያየሩ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሰዎች ምህረት እንዲደረግላቸው ይሆናል።

ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በቀጣዩ የፈረንጆቹ ወርሃ ጥር በ20ኛው ቀን በኦፊሴላዊ በዓለ ሲመታቸው ሥልጣን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሞት ቅጣት የተቀበለው በርናርድ በአሜሪካዋ ኢንዲያና ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 3፡27 ላይ መሞቱ ተነግሯል።

ከቅጣቱ በፊት ረጋ ባለ ሁኔታ ለሦስት ደቂቃ መልዕክት ያስተላለፈው በርናርድ ለፈጸመው ጥፋት ይቅርታ ጠይቋል።

"ይቅርታ። አሁን ያለሁበትን ሁኔታ የሚገልፅልኝ፤ ከዚህ በፊት ያደረግኩትንም የሚገልፅልኝ ቃል ነው" ብሏል ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የሞት ቅጣት ከታሰበለት ሰዓት በላይ ዘግይቷል። ይህም የሆነው የበርናርድ ጠበቆች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ቅጣቱ ይቀልበስ ብለው ይግባኝ በመጠየቃቸው ነው።

የበርናርድ ወንጀል ምን ነበር?

በርናርድ ሰኔ 1999 ዓመተ ምህረት ቶድ እና ስቴሲ ቤግሊ የተባሉ ጥንዶች ግድያ ላይ ተሳትፏል በሚል ነው የተቀጣው።

በርናርድን ጨምሮ አምስት ታዳጊዎች በወቅቱ ጥንዶቹን ከዘረፉ በኋላ በመኪናቸው የኋላ ኪስ ውስጥ አድርገው ሰዋራ ሥፍራ በመውሰድ ተኩሰውባቸዋል፤ ከዚያም በርናርድ መኪናዋን በእሳት አጋይቷል ተብሎ ነው የተከሰሰው።

የበርናርድ ጠበቆች ወንጀሉን የፈፀመው ቪያልቫ በተሰኘው የቡድኑ አለቃ አስገዳጅነት ነው ሲሉ ተከራክረው ነበር።

ቪያልቫ ባለፈው መስከረም በሞት ቅጣት ተቀጥቷል።

ሌሎቹ አባላት ወንጀሉን በፈፀሙ ጊዜ ዕድሜያቸው ከ18 በታች ስለሆነ በእሥር ቅጣት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።

የበርናርድ ጠበቆች ደንበኛቸው በሞት ከሚቀጣ ይልቅ በዕድሜ ልክ እሥራት ሊቀጣ ነው የሚገባው ብለው ቢከራከሩም ጥያቄያቸው በፍርድ ቤት ውድቅ ሆኗል።

በርናርድ በእሥር ላይ ሳለ ምንም ዓይነት ጥፋት አልፈፀመም። አልፎም በእሥር ቤት ፕሮግራም ታቅፎ ሌሎች ሰዎች ወንጀል እንዳይፈፅሙ ሲያስተምር ነበር ሲሉ ጠበቆቹ ተከራክረዋል።

ተዋቂ የአሜሪካ ሴናተሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ግለሰቡ በሞት ቅጣት እንዳይቀጣ ፕሬዝደንት ትራምፕ እንዲምሩት ጠይቀው ነበር።

የሕግ ትምህርት እያጠናች ያለችው አሜሪካዊቷ የቴሌቪዥን ኮከብ ኪም ካርዳሺያንም ግለሰቡ ከሞት ቅጣት እንዲተርፍ ስትወተውት ነበር።

ከትራምፕ ጋር ቅርበት ያላት ኪም ከዚህ በፊት ሌሎች ወንጀለኞች ፍርዳቸው እንዲቀል ለፕሬዝደንቱ ጥያቄ አቅርባ ተሳክቶላት ነበር።