ካናዳ በገፍ የሚደረግ የመድኃኒት ወጪ ንግድን አገደች

ካናዳ በገፍ የሚደረግ የመድኃኒት ወጪ ንግድን ማገዷ ተሰምቷል። በአገሪቷ እጥረት ያጋጥማል በሚልም ፍራቻ ነው በጤና ባለሙያዎች ማዘዣ የሚሸጡ መድኃኒቶች ላይ እገዳ የጣለችው።

አሜሪካ በቅርቡ መድኃኒቶችን ከካናዳ በማስመጣት በቅናሽ ዋጋ ለመሸጥ ማቀዷን ተከትሎ ነው ይህ ውሳኔ የተላለፈው።

ምንም እንኳን በካናዳ ከሌሎች አገራት ጋር ሲወዳደር በጤና ባለሙያዎች ማዘዣ የሚሸጡ መድኃኒቶች ዋጋ ውድ ቢሆንም፤ በአሜሪካ ካለው ግን የቀነሰ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ከካናዳ ለመግዛት ያሰቡት መድኃኒት ክምችትም በአገሪቷ ከፍተኛ እጥረትም እንደሚያስከስትልም የካናዳ መድኃኒት አቅራቢዎችም ሲያስጠነቅቁ ነበር።

የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝን ተከትሎም በአንዳንድ መድኃኒቶች ላይ ያለው የገበያ ፍላጎትም በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል።

ካናዳ 68 በመቶ የሚሆነውን የመድኃኒት ክምችቷን ከአገር ውጭ የምታስገባ ሲሆን በመድኃኒት አቅርቦትም ላይ ችግር ምንም አይነት እክል እንዳያጋጥም መስራት እንደሚገባ የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።

"ኩባንያዎች እጥረት ተከስቷል ወይም ይከሰታል የሚል ስጋት ካላቸው ለመንግሥት ማሳወቅ አለባቸው። ከዚህም በተጨማሪ በ24 ሰዓታት ውስጥ ሊያስከትለው የሚችለውን የጤና ስጋት ገምግመው ሪፖርት ማድረግ አለባቸው" ብሏል የጤና ሚኒስቴሩ መግለጫ።

ዶናልድ ትራምፕ ረከስ ያለ መድኃኒት ከካናዳ እንዲገባ የሚያስችል ትዕዛዝ የፈረሙት በሐምሌ ወር ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ሌሎች አገራትን የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒት ለማቅረብ ያላቸውን ፈቃደኝነት ጠቅሰው ተቀዳሚው ነገር ግን የአገራቸውን ሕዝብ ፍላጎት መጠበቅ ነው ብለው ነበር።

በአሜሪካ ያሉ የመድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች በአዳዲስ መድኃኒቶች ላይ ያለው ውድ ዋጋን እንዲሁም በቀደሙ መድኃኒቶች ላይ የዋጋ ጭማሪን አስመልክቶ ትችቶችን እያስተናገዱ ነው።

እነዚህ ወቀሳዎች በዋነኝነት የመጡት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ ከፖለቲከኞች፣ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ከህመምተኞች ቡድን በኩል ነው።

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም የመድኃኒት ዋጋዎችን ለማውረድ ከሌላ አገር ለማስመጣት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።