ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሴት ፖለቲከኞች ጥምረት የምትመራው ስኬታማዋ ፊንላንድ ስትቃኝ
የዓለም አይን በሙሉ ወደ ፊንላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትርና ጥምር መንግሥታቸው አዙሯል።
ፊንላንድ አምስት ፓርቲዎችን በያዘ በሴቶች ጥምር መንግሥትና በሴት ጠቅላይ ሚኒስትር የምትመራ አገር ናት።
አምስቱም የፓርቲ አመራሮች ሴቶችና ወጣቶች ናቸው።
የጥምር መንግሥቱ አመራሮች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ያሳዩት እርጋታ እንዲሁም ቁርጠኝነት ምስጋና ተችሯቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሳና ማሪን ከሚዲያዎች አፍ አትጠፋም፤ የግል ህይወቷም መወያያ ነው።
የጫጉላ ጊዜዋን በአንድ ሳምንት ብቻ አቋርጣ ስትመጣና ወደ ሥራ ስትመለስ የአገር መሪ መሆን ቀላል አይደለም በሚል ውሳኔ ነበር።
የቀድሞ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋችና የ16 ዓመት የፍቅር ጓደኛዋን ያገባችው ነሐሴ ወር ላይ ነበር።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ባለበት ወቅት ሠርግ መደገሳቸውም መደነቅን ፈጥሯል።
ባለትዳሮቹ ኤማ የምትባል ልጅም አለቻቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሯ ባለቤቷን ማርከስ ራይኮኔንን ከጎኗ ሻጥ ያደረገችበት የሠርግ ፎቶም እንዲሁም ከዚህ ቀደምም ኤማን ስታጠባ የሚያሳዩ ፎቶዎች በኢንስታግራም ገጿ ላይ ማጋራቷ የበርካታዎችን ቀልብ ስቧል።
ባለትዳሮቹ ፈገግ ብለው፣ እጅ ለእጅ ተጠላልፈው ሄልሲንኪ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸውና በተንጣለለው ቪላ ላይም ይታያሉ።
የፖለቲካ መፅሔት አዘጋጆች፣ የፋሽን ጦማሪዎች፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲያው በአጠቃላይ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ፎቷቸውን ተቀባበለውታል።
ከሰሞኑ ደግሞ በርካታ ጋዜጠኞች የሬናይሰንስ ዘመን ሕንፃ በሆነው የፊንላንድ መንግሥት መቀመጫ ተሰባስበው ነበር። የጥምር መንግሥቱ የሚያካሂዱትን ስብሰባ ይጠብቃሉ።
"መናገር የምፈልገውን ነገር ቀድሜ አላዘጋጅም" ትላለች ለቢቢሲ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን ጋዜጠኞቹን እየተጠጋች።
በሴት ጠባቂዎቿም ታጅባ "ስለ ማንኛውም ነገር መጠየቅ ይችላሉ። በአጭሩም እመልሳለሁ።"
በዚህ ሳምንት ምናልባት ብዙው ጥያቄ የግል ህይወቷ ላይ ያነጣጠረ ይሆን? ቢቢሲ ጠቅላይ ሚኒስትሯን የጠየቃት ጥያቄ ነበር።
"አይደለም። በአገሪቷ ውስጥ በርካታ ነገሮች እየተከናወኑ እንደመሆኑ መጠን ስለነሱ ጉዳዮች ማወቅ እንደሚፈልጉ እርግጠኛ ነኝ" በማለት አፅንኦት በመስጠት ከተናገረች በኋላ "መጨረሻ ላይ ምናልባት የግል ህይወቴ ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን ይጠይቁ ይሆናል" ብላለች።
አንዳንዶቹ ሪፖርተሮች ጭምብላቸውን አጥልቀዋል። ትልልቅ ማይክራፎንም የያዙም ነበሩ። የተሰበሰቡትን ሪፖርተሮች ስትጠጋቸውም የሁሉም ቀልብ እሷ ላይ አተኮረ።
ለስብሰባው ከሁሉም ቀድማ የደረሰችው የመጀመሪያ ፖለቲከኛ እሷ ነበረች። ልክ ብላለች የፊንላንድ ሚዲያ አገሪቷ ላይ ስላለሉት አንገብጋቢ ጉዳዮች ጥያቄዎችን ማዥጎድጎድ ጀመሩ።
ከዚያም ወደ ስብሰባዋ አቀናች። አራት ሰዓታት ከፈጀው ስብሰባ በኋላም ለጋዜጠኞች ጥያቄዎች ለመመለስ ቆመች።
ወደ ቤቷ ለመሄድም የመጨረሻዋ ፖለቲከኛ ነበረች።
የጠቅላይ ሚኒስትሯ የመጀመሪያ ፎቶ በዓለም ዘንድ መነጋገሪያ የሆነው ሥራዋን 'ሀ' ብላ በጀመረችበት ወቅት በአውሮፓውያኑ ታኅሳስ 2019 ነበር።
በወቅቱ የ34 ዓመቷ ጠቅላይ ሚኒስትር የግራ ዘመም ጥምር ፓርቲዋ መሪ ፖለቲከኞች ጋርም ፈገግ ብላ የተነሳችው ነው።
ከአምስት ፓርቲዎች የተውጣጣው ጥምር ፓርቲ መሪዎች መካከል በወቅቱ እንደኛዋ ብቻ ናት ከ34 ዓመት በላይ የሆነችው።
በምክር ቤቱ መድረክ ላይ ባደረገችው ንግግርም "የወጣቱ ትውልድ ተወካይ ነኝ" አለች።
ዓለም አቀፉ ሚዲያም በፊንላንድ ላይ ማተኮሩን እንደ በጎ ተግባር እንደምትመለከተው ተናገረች። "ለቀሪው ዓለም ፊንላንዳውያን ምን አይነት ህዝቦች እንደሆን ለማሳወቅም እድል ይፈጥርልናል" አለች።
በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በፖለቲከኞች ደረጃ ብቻ አይደለም እውቅናን ያተረፈችው።
'ሬጅ ኤጌይንስት ዘ ማሺን' የተባለው የአሜሪካ ሮክ ባንድ ጊታር ተጫዋች ቶም ሞሬሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን አድናቂያችን ናት በማለት የጥምር ፓርቲውን ፎቶ በኢንስታግራም ገፁ ላይ ለጠፈ።
እሷም በምላሹ ያው እንደ ዘመኑ ፎቶውን በመውደድ (ላይክ በማድረግ) ያላትን አድናቆት ገለፀች።
ሚዲያዎችም "ፌሚኒዝም የደረሰበትን ደረጃ በማወደስ፣ የፊንላንድ ፓርላማና የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ፈር ቀዳጅ፣ ስንጠብቀው የነበረው የሴቶች አገዛዝ" በማለትም መፃፍ ጀመሩ።
አንዳንዶችም ጥምሩን መንግሥት በማንቋሸሽ ፆተኛ በሆነ መንገድ አመራሮቹ ሳውና ውስጥ ገብተው ሲታጠቡ የሚያሳይ ምስል ይዘው የወጡ አልታጡም።
ሆኖም ቀረም ፊንላንድ የፌሚኒስት "ዩቶፕያ"፣ ደሴት ናት ተባለች። ፊንላንድ ግን ሴት ዜጎቿን ከወንድ እኩል አድርጋ ማየትና እድል መስጠት የጀመረችው አሁን አይደለም።
በዓለም ታሪክም ሴቶች እንዲመርጡም ሆነ በፓርላማ ድምፅ እንዲኖራቸውም ፈር ቀዳጅ ናት ፊንላንድ።
በርካታ ምዕራባውያን አገራት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ቢሆንም ሴቶች እንዲመርጡ የፈቀዱት፤ ፊንላንድ ግን በአውሮፓውያኑ 1906 ነው።
በቀጣዩም ዓመት 19 ሴቶች ለፓርላማ አባልነት ተመረጡ። በአውሮፓውያኑ 2000 የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንት ታርጃ ሃሎኔን መረጠች።
ከሦስት ዓመታት በኋላ፣ በ2003 አኔሊ ጃቴንማኪ የመጀመሪያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆና ተመረጠች። ከዚያም በኋላ ሌላ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበራት ፊንላንድ በ2019ም በዕድሜ ትንሿ የሆነችውን ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪንን መረጠች።
ስልጣኑን የተቀበለችው ከጠቅላይ ሚኒስትር አንቲ ሪን ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፖስታ ቤት የተነሳውን የሥራ ማቆም አድማ መቆጣጠር ባለመቻሉም ነው እሷ የተመረጠችው። የግራ ዘመሙ የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ በእድሜ ትንሽ የሆነችውን ማሪንን ይመርጣል ብሎ አልጠበቀም ነበር።
ሳና ማሪን ቢቢሲ በዚህ ዓመት ተፅእኖ ፈጣሪ ብሎ ካካተታቸው 100 ሴቶች አንዷ ናት
የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነው ብሎ ሲያውጅ በጠቅላይ ሚኒስትር ማሪን የሚመራው ምክር ቤቱ ለቫይረሱ ተዘጋጅቶ ነበር።
ድርጅቱ ወረርሽኙን ባሳወቀ በቀናት ውስጥ ፊንላንድ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴን ማገድ ብቻ ሳይሆን ለጦርነት የምትጠቀምበትን ድንገተኛ የተባለውን 'ኢመርጀንሲ ፓወርስ አክት' ተግባራዊ አደረገች።
ይህንን መመሪያ አገሪቱ የተጠቀመችበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሲሆን ለሠራተኞች የሚከፈለውን ደመወዝ ጨምሮ፣ ተጨማሪ ሠራተኞችን በተለያዩ አገልግሎት ማሰማራትም ይገኝበታል።
መመሪያው በተለያዩ ሚዲያዎች ቢወገዝም ሕዝቡ ግን ደግፎት ነበር። የፊንላንድ ዜጎች በቤታቸው እንዲወሰኑ፣ ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች እንዲመረመሩና ተከታታይ የበይነ መረብ ክትትሎችም ተጠናከሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪንና አራት ከፍተኛ የምክር ቤቱ አባላት በየሳምንቱ ስለ ኮሮናቫይረስ መግለጫ ይሰጣሉ፤ ከሚዲያም ሆነ ከዜጎች ጋር ውይይትና ጥያቄና መልስ ያካሂዳሉ። ከህፃናትም ጋር እንዲሁ።
ከታይዋን፣ ጀርመንና ኒውዚላንድ መሪዎች ጋር በመደመር ተወደሰች። በዓለም ላይም ሴት መሪዎች የበለጠ ቀውሱን መቆጣጠር ችለዋልም የሚል ስም አሰጣቸው።
5.5 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ፊንላንድ በኮሮናቫይረስ የሞተባት ሰው ቁጥር 370 ብቻ ነው። መሪዋ እንደሚሉት መንግሥታቸው በሳይንስ የተመሰረተ መመሪያዎችን ከመጠቀም በተጨማሪ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን መከተሉ ከዚህ ወረርሽኝ ለመውጣት እንደጠቀማቸውም ይናገራሉ።
በሚዲያዎች ሲወቀስ የነበረው ኢመርጀንሲ አክት በሰኔ ወር ቢነሳም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የሴንተር ፓርቲ መሪ የ33 ዓመቷ ካትሪ ኩሉሙኑ ከስልጣን መልቀቋ አመራሩን በተወሰነ መልኩ አብረከረከው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከገንዘብ ቅሌት ጋር በተያያዘም ነበር የለቀቀችው። በእሷ ቦታ አኒካ ሳሪኮ ተተካች። ጥምር ፓርቲው በይፋ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ስምምነት ላይ ያለ ቢመስልም በፓርቲዎቹ መካከል አለመግባባትም ነበር ተብሏል።
በታዳጊነቷ ጠቅላይ ሚኒስትርነትም ሆነ በፖለቲካው እሳተፋለሁ የሚል የሩቅ ህልምም አልነበራትም።
እንደ በርካታ ፊንላንዳውያን "አሳዛኝ የቤተሰብ ታሪክ ነው ያለኝ" በማለትም ከአራት ዓመት በፊት የግል ህይወቷን በፃፈችበት ጦማር ላይ አስፍራለች።
በፊንላንድ ደቡብ ምዕራብ በምትገኝ ፒርካላ በምትባል ትንሽ መንደር ነው ያደገችው።
ያደገችውም ከእናቷና ከእናቷ የህይወት አጋር ነው። ምንም እንኳን በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ቤተሰብ ውስጥ ማደጓ ነፃነትን ቢፈጥርላትም በከፍተኛ የገንዘብ ጫና ውስጥ እንደነበሩ ትናገራለች።
በማደጎ ውስጥ ያደገችው እናቷ ከሰካራም ባለቤቷ፣ ከማሪን አባት ጋር መፋቷቷን ተከትሎም ከመንግሥት በሚሰጣት ድጎማ ነበር የምትኖረው።
ሳና ማሪንም ቤተሰቡን ለመደገፍ ገና በልጅነቷ የሥራውን ዓለም ተቀላቀለች። በትምህርቷ ይህ ነው የሚባል አመርቂ ውጤትም አታሳይም ነበር። ፓሲ ኬርቪኔን የተባለች የሁለተኛ ደረጃ መምህሯም "መካከለኛ ተማሪ " ነበረች ብላለች።
የፖለቲካ ህይወቷ የተጠነሰሰው በሃያዎቹ እድሜ ላይ እያለች ነው። የእሷንም ብቻ ሳይሆን በአካባቢዋ ያሉትንም መቀየር እንደሚቻል ተረዳች።
ለጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን የእኩልነት ፕሮግራም መነሻው ይህ ነው።
ቤተሰቦች ልጆቻቸውን የመንከባከብ ኃላፊነት በእኩልነት እንዲወጡ በፖሊሲ ደረጃ ማርቀቅ፣ የቤት ውስጥ ጥቃትን ለመከላከል ከፍተኛ ቅጣት መጣል፣ በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የክፍያ ልዩነት ማስቀረት እንዲሁም ከደሃና ስደተኛ ቤተሰቦች ለሚመጡ ህፃናት የትምህርት እድል መስጠት መንግሥቷ የሚጠቅስላት አመርቂ ሥራዎች ናቸው።
እንዲሁም በፆታዊ ማንነት ጋርም በተያያዘ እኩልነት መስፈን አለበትም ትላለች።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሰራችው ሥራ በሕዝቧ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀባይነት የጨመረ ቢሆንም ከዓለም አቀፉ ብላክ ላይቭስ ማተር እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ መንግሥቷ ትችቶችን አስተናግዷል።
ምንም እንኳን በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያለውን ኢ-ፍትሃዊነት ለመቅረፍ መንግሥት ቢሰራም ጥቁሮች ላይ ያለውን ጫና ቦታ አልሰጠም በማለት ጥቁር ፊንላንዳውያን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወቅሰዋል።
በፊንላንድ ውስጥ ከሚኖሩ ጥቁሮች መካከል 63 በመቶ የሚሆኑት ተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት እንደሚደርስባቸውም የአውሮፓ ካውንስል ከሁለት አመታት በፊት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል፤ ይህም በአውሮፓ ከፍተኛው ነው።
በፊንላንድ ፓርላማም ውስጥ አንዲት ጥቁር ሴት ብቻ መሆኗ አገሪቷ ገና ከፍተኛ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃት አሳይ ነው ተብሏል።