የአሜሪካ ምርጫ፡ አሸናፊውን እስካሁን ያላወቅነው ለምንድነው?

የአሜሪካ ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካውያን እንዲህ ባለ መልኩ በንቃትና በከፍተኛ ቁጥር ሲሳተፉበት በቅርብ ዓመታት አልታየም በተባለው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕና ጆ ባይደን አስስከመጨረሻዋ ሰዓት አንገት ላንገት ተናንቀዋል።

ለመሆኑ በምርጫው አሸንፎ ፕሬዝደንት የሚሆነው ማነው? ይህ ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም። ጆ ባይደንም ሆነ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

እንደውም በኮሮረናቫይረስ ምክንያት በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ የተባለ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በፖስታ በኩል ድምጻቸውን መላካቸውን ተከትሎ የምርጫ ቆጠራውና ይፋዊ ውጤቱ ከዚህ በኋላ ቀናት ሊፈጅ እንደሚችል ይገመታል።

እንደ አሪዞና፣ ጆርጂያ እና ፔንሲልቬኒያ ያሉ ወሳኝ ግዛቶች ዛሬ ውጤት ይፋ እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ነው።

የእነዚህ ግዛቶች አጠቃላይ ውጤትና በቀላሉ ተፎካካሪዎቹ ያሸንፉባቸዋል ተብሎ የሚገመቱ ግዛቶችን ውጤት ከግምት ውስጥ አስገብቶ እንኳን ማን ያሸንፋል? የሚለውን ለማወቅ ምናልባት እስከ አርብ ድረስ መጠበቅ ግድ ሊል ይችላል።

ነገር ግን ይሄ ብቻ አይደለም አሳሳቢው ጉዳይ። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በውጤቱ ደስተኛ እንዳልሆኑና 'ምርጫው ሊጭበረበር' እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ምናልባት ፕሬዝዳንቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የሚወስዱት ከሆነ ደግሞ የ2020 አሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊን ሳናውቅ ሳምንታት ልንቆይ እንችላለን።

ወሳኞቹ ግዛቶች

በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ የበርካቶችን ድምጽ ማግኘት ብቻ በቂ አይደለም።

በኢሌክቶራል ኮሌጅ የምርጫ ሥርዓት መሠረት ሁለቱም ተፎካካሪዎች ካሉት 538 ድምጾች ቢያንስ 270 ማግኘት አለባቸው።

በዚህ የምርጫ ስርአት መሰረት እያንዳንዱ ግዛት ባለው የህዝብ ብዛት መሰረት ድምጽ ያገኛል።

በርካታ ነዋሪዎች ያሏቸው ግዛቶች ከፍተኛ ድምጽ ያላቸው ሲሆን፤ ለምሳሌ ፔንሲልቬንያን ያሸነፈ ተፎካካሪ 20 ድምጾችን ያገኛል ማለት ነው።

ዝቅተኛ የሚባል ድምጽ ካላቸው ግዛቶች ማካከል ደግሞ እነ ሞንታና፣ ኖርዝ ዳኮታ እና ሳውዝ ዳኮታ ይጠቀሳሉ።

በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ድምጽ የሚገኝባቸው ግዛቶች ወሳኞቹ የፍልሚያ ቦታዎች ተብለው ይጠራሉ።

የአሜሪካ ምርጫ በቅድመ ትንበያ የተሞላ ነው። የግል ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን ሕዝቡን 'እንደው ማንን ለመምረጥ አስባችኋል?' ብለው ይጠይቁና ውጤት ይተንብያሉ።

በዚህ ቅድመ ትንበያ መሠረት ደግሞ ባይደን የአሜሪካውን ምርጫ ተደላድለው እንደሚያሸንፉ ተገምቶ ነበር።

ነገር ግን ባለፈው የ2016 ምርጫ እንዲሁ ትንበያ ተሰርቶ ሂላሪ ክሊንተን ያሸንፋሉ ቢባልም ውጤት ሲመጣ ግን ብዙዎች ያልጠበቁት ሆኖ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት መሆን ችለዋል።