የአሜሪካ ምርጫ፡ ምን ዜና ልንሰማ እንችላለን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በስተመጨረሻም እንዳይደርሱት የለ ጊዜው ደርሷል። የመጨረሻው መጨረሻ። በጉጉት የተጠበቀው የአሜሪካ ምርጫ ቁርጡ ሊለይለት ነው።
የዘንድሮው ምርጫ እንደሌሎቹ ጊዜዎች አይደለም። ግራ አጋቢ ዜናዎች የተሰሙበት፣ የሚጠብቁት ቀርቶ የማይጠብቁት የሚሆንበት ነው የዘንድሮው።
የአሜሪካ ምርጫ ልክ እንደ ሃብታም ድግስ አንድ ቀን የሚበቃው አይደለም። መራጮች ድምፅ መስጠት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ከ90 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ድምፃቸውን እኮሮጆው አስገብተዋል።
ታድያ ስለ አሜሪካ ምርጫ ምን ዓይነት ዜና ይጠብቀን ይሆን? ሶስት ተጠባቂ ዜናዎች አሉ።
አንደኛ፡ ባይደን በቀላሉ አሸነፉ
የአሜሪካ ምርጫ በቅድመ ትንበያ የተሞላ ነው። የግል ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን ሕዝቡን 'እንደው ማንን ለመምረጥ አስባችኋል?' ብለው ይጠይቁና ውጤት ይተንብያሉ።
በዚህ ቅድመ ትንበያ መሠረት ባይደን የአሜሪካውን ምርጫ ተደላድለው ማሸነፍ አለባቸው።
ነገር ግን ባለፈው ምርጫ እንዲሁ ትንበያ ወጥቶ ሂላሪ ክሊንተን ያሸንፋሉ ቢባልም ውጤት ሲመጣ ግን ብዙዎች ያልጠበቁት ሆኗል።
ቢሆንም የዘንድሮው ትንበያ ከባለፈው ጊዜ በተለየ ፍፁም ነው የሚሉ አልጠፉም።
ትንበያው ባይደንን በሃገር አቀፍ ደረጃ አናት ላይ አስቀምጧቸዋል።
እንግዲህ ይህን መሠረት አድርገን ልንሰማቸው ከምንችላቸው ዜናዎች አንዱ ይህ ነው ብንል ማበል አይሆንም።
ሁለተኛ፡ ትራምፕ በአስደንጋጭ ሁኔታ አሸነፉ
ለምን በአስደንጋጭ መልኩ ካሉ ምክንያቱም ትንበያው የሚለው ሌላ ስለሆነ እንሎታለን።
የአሜሪካ ዜና አውታሮች ትራምፕ ምርጫውን ከረቱ 'ቅድመ ትንበያው አሁንም ተሳስቷል' ከማለት የሚቆጠቡ አይመስሉም።
ትራምፕ በፍሎሪዳና ፔኒሲልቬኒያ ግዛቶች ማሸነፍ ከቻሉ ሁኔታውን ለጆ ባይደን ሊያከብዱባቸው ይችላሉ።
ትራምፕ፤ እንደውም ከባለፈው ምርጫ በተሻለ በላቲን አሜሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት አላቸው እየተባለ ነው። ይህ ደግሞ ፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ ትልቅ ሃብት ነው።
በሌላ በኩል ፔኒሲልቬኒያ ግዛት በርካታ ነጭ ሠራተኛ መደብ ሰዎች የሚኖሩባት ስለሆነች ለትራምፕ አደጋ ልትሆን ትችላለች።
ሶስተኛ፡ ጆ ባይደን በሰፊ ልዩነት አሸነፉ
እርግጥ ነው ቅድመ ትንበያው ጆ ባይደን ያሸንፋሉ ይላል። ነገር ግን በጠባብ ውጤት እንደሆነ ነው የሚጠቁመው።
ሶስተኛው ዜና ግን ምናልባት ጆ ባይደን ቅድመ ትንበያውን ጥሰው በሰፊ ውጤት ማሸነፋቸውን የሚናገር ሊሆን ይችላል።
ይህ ከሆነ ፕሬዝደንት ትራምፕን ጉድ የሰራቸው ኮሮናቫይረስ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ባለፈው ምርጫ ትራምፕ ግልፅ መልዕክት ነበር ይዘው የቀረቡት። የግንብ አጥር እገነባለሁ ብለዋል፤ ሙስሊሞችን ወደ ሃገሬ አላስገባም ከማለት አልቦዘኑም፤ ስለ ንግድም ቁልጭ ያለ ዕቅድ ነው ይዘው የቀረቡት።
በዘንድሮው ግን እዚህ ግባ የሚባል ዕቅድ የሌላቸው ሰው ሆነው ታይተዋል።
ይህ ለጆ ባይደን ያላሰቡት ፍርቱና ሊሆናቸው እንደሚችል ፖለቲካ የሚበልቱ ሰዎች ይናገራሉ።












