የዶናልድ ትራምፕ ሕይወት፡ ከሆቴል እስከ ቤተ መንግሥት

የትራምፕ ቤተሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ምርጫ ዕጩ ሆነው ከመቅረባቸው በፊት እጅግ የታወቁ ቢሊዮነር ነበሩ።

አንድ ቀን ፕሬዝደንት እሆናለሁ ብለውም ይናገሩ ነበር። ይኸው አሁን አሜሪካን እየመሩ ይገኛሉ።

ፕሬዝደንቱ በዕጩነት ሲቀርቡ 'አሁንስ እኒህ ሰውዬ አበዙት' ያላለ አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ ሰውዬው ከዚያ በፊት የሚታወቁበት ባህሪያቸው ነው።

ነገር ግን የ70 ዓመቱ የንግድ ሰው የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ሆነው ወደ መድረክ ወጡ።

በአሜሪካ ታሪክ እጅግ አነጋጋሪውና አከራካሪው ነው የተባለውን የ2016 ምርጫ ረትተው መንበረ ሥልጣን ተቆናጠጡ።

አሁን ድጋሚ ለመመረጥ ሌላ አወዛጋቢ ምርጫ ውስጥ ይገኛሉ።

የልጅነት ሕይወት

ዶናልድ ኒው ዮርክ ውስጥ በመኖሪያ ቤት ሽያጭ እጅግ የናጠጡት ፍሬድ ትራምፕ አራተኛ ልጅ ናቸው።

በአባታቸው ኩባንያ ውስጥ አንድ አነስተኛ የሚባል ሥራ ተሰጥቷቸው እንዲሠሩ ቢጠበቁም ትምህርት ቤት ውስጥ በጥባጭ ፀባይ በማሳየታቸው ወደ ወታደራዊ አካዳሚ ተላኩ።

ታላቅ ወንድማቸው ፍሬድ ፓይለት ሲሆኑ ጊዜ የአባታቸውን ንብረት ለመቆጣጠር ዶናልድ ያኮበክቡ ጀመር።

ታላቅ ወንድሜ ፍሬድ በ43 ዓመታቸው በአልኮል መጠጥ ምክንያት ሲሞት ነው አልኮልና ትምባሆ ንክች ላለማድረግ የወስንኩት ይላሉ ትራምፕ።

ትራምፕ ወደ 'ሪል ስቴት' ዘርፍ የገቡት ከአባታቸው አንዲት ሚሊዮን ብር ተበድረው እንደሆነ ይናገራሉ። ቀስ በቀስ የአባታቸውን ትላልቅ 'ፕሮጀክቶች' ማንቀሳቀስ ያዙ።

በአውሮፓውያኑ 1971 የአባታቸውን ድርጅት ስም 'ትራምፕ ኦርጋናይዜሽን' ሲሉ ሰየሙት።

የትራምፕ አባት የሞቱት በ1999 [በአውሮፓውያኑ] ነበር። ትራምፕ 'አባቴ ለኔ መነቃቃቴ ነው' ብለው ነበር በወቅቱ።

የቢዝነስ ሕይወት

ትራምፕ የቤተሰባቸውን ቢዝነስ ከአነስተኛ ከተሞች ጀምሮ እስከ ትላልቆቹ ድረስ በማስፋፋት ይታወቃሉ።

አሜሪካ ውስጥ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ትራምፕ ህንፃ የሚል ማየት እንግዳ አይደለም። ሙምባይ፣ ፊሊፒንስና ኢስታንቡል ውስጥም ትራምፕ ታወር የተሰኙ ሕንፃዎች አሏቸው።

ትራምፕ ሆቴሎችና ቁማር ቤቶችም ገንብተዋል። ነገር ግን ይህ ማስፋፋት የባንክ ዕዳ ውስጥ እንደከተታቸው ይነገራል።

አልፎም አሜሪካና የተቀረው ዓለም የሚዘጋጁ የቁንጅና ውድድሮች ባለቤት ነበሩ።

ወይዘሪት ዓለም፣ ወይዘሪት ዩኤስኤ፣ እንዲሁም ወይዘሪት ታዳጊ ዩኤስኤ የቁንጅና ውድድሮች ባለቤት የእሳቸው ድርጅት ነበር።

በ2003 ኤንቢሲ የተሰኘው ጣቢያ ላይ 'ዚ አፕሬንቲስ' የተሰኘ ኢ-ልቦለዳዊ የቴሌቪዥን ቅንብር ጀመሩ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ሆነው ለ14 ዓመታት ሠርተዋል። ትራምፕ 213 ሚሊዮን ዶላር ለዚህ ተግባሬ ተከፍሎኛል ይላሉ።

ትራምፕ በርካታ መፃሕፍትንም ፅፈዋል።

ድርጅቶቻቸው ከክራባት ጀምሮ እስከታሸገ ውሃ ድረስ ያመርታሉ፤ ይሸጣሉ።

ፎርብስ መፅሔት የትራምፕ ሃብት 3.7 ቢሊዮን ዶላር ነው ቢልም እሳቸው ግን 10 ቢሊዮን ዶላር ነው ይላሉ።

አባትና ባል

ትራምፕ ሶስት ጊዜ አግብተዋል፤ ሁለት ጊዜ ፈትተዋል።

ታዋቂዋ የቼክ አትሌት ኢቫና ዜልኒኮቫ የመጀመሪያ ሚስታቸው ነበረች። ከኢቫና ጋር ሶስት ልጆች አሏቸው። ዶናልድ ትንሹ፣ ኢቫንካና ኤሪክ።

ከኢቫና በመቀጠል ተዋናይት ማርላ ማፕልስን አገቡ። ከ6 ዓመት ትዳራቸው ቲፋኒ የተሰኘች ሴት ልጅ አግኝተዋል።

ከዚያ በመቀጠል የአሁኗ ባለቤታቸው ቀዳማዊ እመቤት ሜላኒያን አገቡ። ይህ የሆነው 2005 ላይ ሲሆን በወቅቱ ሜላኒያ ሞዴል ነበረች።

ሜላኒያና ትራምፕ ባሮን ዊሊያም የተሰኘ ልጅ አላቸው።

ትራምፕ አሁንም የድርጅታቸው ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢሆኑም ከመጀመሪያ ትዳራቸው ያፈሯቸው ልጆች ድርቶቻቸውን ያስተዳድሩላቸዋል።

ዕጩ

ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የመሆን ህልም እንዳለቸው መናገር የጀመሩት ከ1987 ጀምሮ ነው።

በ2000 በተካሄደው ምርጫ ላይ የሪፎርም ፓርቲ አባል ሆነው ተወዳድረው ነበር።

በ2008 ባራክ ኦባማ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ትራምፕ፤ 'ኦባማ የተወለዱት አሜሪካ' አይደለም ሲሉ ተደመጡ። ነገር ግን ይህ የትራምፕ ፅንሰ ሐሳብ ሃሰት ነበር።

ትራምፕ ይቅርታ ባይጠይቁም ፅንሰ ሐሳባቸው ሃሰት መሆኑን አምነዋል።

ትራምፕ በይፋ የምርጫ ዘመቻውን የተቀላቀሉት ሰኔ 2015 ነበር። 'አሜሪካን ድጋሚ ታላቅ አደርጋታለሁ' ሲሉ ነበር ዘመቻቸውን የጀመሩት።

የሰውዬው የምረጡኝ ዘመቻ እጅግ አነጋጋሪ ነበር።

'በሜክሲኮና በአሜሪካ ድንበር ላይ የግንብ አጥር እዘረጋለሁ፤ ሙስሊሞች ወደ ሃገሬ እንዳይገቡ አግዳለሁና የአሜሪካን ምጣኔ ሃብት አጠናክራለሁ' በሚሉ ንዑስ ሐሳቦች ነበር ደጋፊዎቻቸውን መግዛት የቻሉት።

ትራምፕ በዚህ አቋማቸው ብዙ ተቃውሞዎች ገጥሟቸው ነበር። እሳቸው ግን 'ፍንክች' አላሉም።

ትራምፕ የምርጫውን ዘመቻውን ከመቀላቀላቸው በፊት አድርገዋቸዋል የተባሉ እኩይ ተግባሮቻቸው በሚድያ ቢናፈሱም ለደጋፊዎቻቸው ግን ይህ የኔን ስም ለማጥፋት የተወጠነ ነው በማለት ያስተባብሉ ነበር።

ለአንዳንድ ሰዎች ትራምፕ ያለፈውን ምርጫ ማሸነፋቸው አሁንም ያስገርማቸዋል።

ትራምፕ ያለ ምንም የፖለቲካ ልምድና የውትድርና ሥልጠና መንበር የጨበጡ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ናቸው።