የአሜሪካ ምርጫ፡ ምርጫውን በቀላሉ መረዳት የሚያስችሉ ነጥቦች

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከአሜሪካ ዜጎች በተጨማሪ የበርካቶችን ሕይወት የሚነካ ስልጣን አለው።
ጥቅምት 24 ደግሞ የምርጫ ካርዳቸውን የወሰዱ አሜሪካውያን ዶናልድ ትራምፕን አልያም ጆ ባይደንን ፕሬዝዳንታቸው አድርገው ለመምረጥ ድምጻቸውን የሚሰጡበት ቀን ነው።
የምርጫው ውጤት ሁሉንም ይመለከታል።
የአሜሪካ የፖለቲካ ስርአት በሁለት ፓርቲዎች የበላይነት የሚመራ ነው። ስለዚህ የሚመረጠው ወይም የምትመረጠው ፕሬዝዳንት ከሁለቱ ፓርቲ የአንዱ አባል መሆን አለባቸው።
ሪፐብሊካኖች ወግ አጥባቂ የፖለቲካ ፓርቲ ሲሆኑ የዘንድሮው እጩ ደግሞ የአሁኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው።
በአሁኑ ሰአት የሚወዳደሩትም ለሁለተኛ ዙር ፕሬዝዳንት ለመሆን ነው። ካሸነፉ ለተጨማሪ አራት ዓመታት አሜሪካን ይመራሉ ማለት ነው።
በቅርብ ዓመታት ሪፐብሊካኖች ዝቅተኛ ግብር አንዲኖር፣ ከፍተኛ ቁጥጥር በጦር መሳሪያዎች ላይ አንዲደረግና ስደተኞችን በተመለከተ ጠበቅ ያለ ሕግ እንዲወጣ ሲሰሩ ነበር።
ፓርቲውም በገጠራማ የአሜሪካ ክፍሎች ከፍተኛ ተቀባይነትና ድጋፍ ያለው ሲሆን እንደ ጆርጅ ቡሽ፣ ሮናልድ ሬገን እና ሪቻርድ ኒክሰንን የመሳሰሉ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶችም በነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ ድጋፍ ነበራቸው።
ዴሞክራቶች ደግሞ ተራማጅ የሚባል ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ናቸው።
በዘንድሮው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ደግሞ ፓርቲውን ወክለው ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የሚወዳደሩት የብዙ ዓመታት ፖለቲካዊ ልምድ ያላቸውና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ምክትል የነበሩት ጆ ባይደን ናቸው።
ዴሞክራቲክ ፓርኪ ከሲቪል መብት፣ ኢሚግሬሽን እና የአየር ጸባይ ለውጥን በተመለከተ ባለው ተራማጅ አስተሳሰብ ይታወቃል። ፓርቲው መንግስት እንደ ጤና መድህን መሳሰሉ ነገሮችን በማሟላት የህዝቡ የእለት ተእለት ሕይወት ላይ ከፍተና ሚና መጫወት እንዳለበት ያምናል።
ከሪፐብሊካኖች በተቃራኒው መልኩ ዴሞክራቶች በርካታ ደጋፊዎቻቸው የሚገኙት ከተማ ቀመስ በሆኑ የአሜሪካ አካባቢዎች ነው።
እንደ ጆን ኤፍ ኬኔዲ እና ባራክ ኦባማን የመሳሰሉት ፕሬዝዳንቶችም በነዚሁ አካባቢው ድጋፍ ነበራቸው።
በዘንድሮው ምርጫ ላይ የሚፎካከሩት እጩዎች ዕድሜያቸው 70 ዓመትን የተሻገረ ሲሆን፤ ትራምፕ ካሸነፉ በ74 ዓመታቸው ለፕሬዝዳንትነት ይዘጋጃሉ።
ጆ ባይደን እድል ከቀናቸው ደግሞ በ78 ዓመታቸው ፕሬዝዳንት በመሆን በአሜሪካ ታሪክ በእድሜ የገፉት ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።
አሸናፊውእንዴትነውየሚታወቀው?
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ለማሸነፍ ብዙ ድምጽ ማግኘት ብቻ በቂ አይደለም። በኢሌክቶራል ኮሌጅ የምርጫ ሥርዓት መሠረት ሁለቱም ተፎካካሪዎች ካሉት 538 ድምጾች ቢያንስ 270 ለማግኘት ነው እየታገሉ ያሉት።
በአሜሪካ ምርጫ ለማሸነፍ ወሳኝ የሚባሉ ግዛቶች አሉ። ፕሬዝደንታዊ ዕጩዎች እነዚህን ግዛቶች ለማሸነፍ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ያደርጋሉ።
የአሜሪካ ግዛቶች የሕዝብ ብዛታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በአጠቃላይ 538 ድምፆች ተከፋፍለው ይዘዋል።
ነገር ግን እኒህ ድምፆች ለ50ዎቹ ግዛቶች እኩል የተከፋፈሉ አይደሉም። የምርጫ አውድማ የሚባሉት እኒህ ግዛቶች ከሌሎች ግዛቶች የበለጠ ድምፅ አላቸው።
እስካሁን ድረስ የተሰበሰቡት ድምፆች እንደሚጠቀሙት ባይደን በሚቺጋን፣ ፔንሲልቫኒያ እና ዊስኮንሲን ግዛቶች የተሻለ ተቀባይነት አላቸው። ትራምፕ ከእነዚህ ግዛቶች በሰበሰቡት ድምፅ ነው በጠባብ ውጤት ያለፈውን ምርጫ መርታት የቻሉት።
ጆ ባይደን፤ በእነዚህ ግዛቶች ብቻ ሳይሆን ባለፈው ምርጫ የትራምፕ ናቸው ተብለው በነበሩት ኦሃዮና ቴክሳስ ግዛቶችም የተሻለ ተቀባይነት አግኝተዋል።
በነዚህ ግዛቶች የሪፐብሊካን እና ዴሞክራት ደጋፊዎች እኩል በሚባል ደረጃ ይገኛሉ።
ከዚህ በፊት የሪፐበሊካኖች ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩት እንደ አሪዞና እና ቴክሳስ ያሉ ግዛቶች በዘንድሮው ምርጫ ከፍተኛ ትንቅንቅ እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።
ምክንያቱም በዘኒህ ግዛቶች ዴሞክራቶችም ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኙ በመምጣታቸው ነው።
ማን መምረጥ ይችላል? እንዴትስይመርጣል?
እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም ዜጋ በየአራት ዓመቱ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ መሳተፍ ይችላል።
ነገር ግን በርካታ ግዛቶች ዜጎች ከመምረጣቸው በፊት ማንነታቸውን መግለጽ የሚችል መታወቂያ እንዲያቀርቡ ያስገድዳሉ።
እነዚህ ሕጎች በብዛት የተቀመጡት በሪፐብሊካኖች ሲሆን፤ ምክንያታቸውም የምርጫ መጭበርበርን ለመከላከል የሚል ነው።
ዴሞክራቶች ደግሞ ደሃ እና ጭቁን የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ድምጽ ለማፈን ሆን ተብሎ የተቀመጠ ሕግ ነው በማለት ይከሳሉ።
ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የዘንድሮው ምርጫ በርካታ የተዘበራረቁ ነገሮችን አስተናግዷል።
አንዳንድ ፖለቲከኞች ህዝቡ በፖስታ ቤት በኩል የምርጫ ድምጹን እንዲሰጥ የጠየቁ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በፖስታ ቤት መምረጥ ለመጭበርበር ያጋልጣል ሲሉ ተደምጠዋል።
እስካሁን ከ90 ሚሊየን በላይ ሰዎች በፖስታ ቤት በኩል ከወዲሁ ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን፤ በአገሪቱ ታሪክ በፖስታ ይህን ያክል ቁጥር ያለው ዜጋ ሲመርጥ ይህ ከፍተኛው ነው።
በዘንድሮውምርጫፕሬዝደንትብቻነውየሚመረጠው?
በዘንድሮው ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን ብቻ አይደሉም የሕዝብ ድምጽ የሚሰጣቸው።
ሁለቱም ፓርቲዎች (ሪፐብሊካን እና ዴሞክራት) የአሜሪካ ምክር ቤት ምርጫን በትኩረት ነው የሚከታተሉት።
በአሁኑ ሰዓት በምክር ቤቱ ሪፐብሊካኖች ከዴሞክራቶች በሦስት ወንበር አብላጫ ወስደዋል።
የትራምፕ ወዳጅ የሆኑት ሊንዚ ግራሃም በደቡብ ካሮላይና በሕይወታቸው አይተውት የማያውቁት ፖለቲካዊ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።
ተቀናቃኛቸው ደግሞ ዴሞክራቱ ጄሚ ሃሪሰን ናቸው።
ምንም እንኳን ሊንዚ ግራሃም ከ2003 ጀምሮ በምክር ቤቱ ወንበር ተቆናጥጠው የቆዩ ቢሆንም ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ባላቸው ድጋፍ ምክንያት ግን የአንዳንድ መራጮችን ድምጽ አጥተዋል።
በዘንድሮው ምርጫ ሌሎች ነገሮችም የሕዝብ ድምጽ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ የዕጸ ፋርሰ ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪያ ነው።
በአሪዞና፣ ሞንታና፣ ኒው ጀርሲ እና ሳውዝ ዳኮታ መራጮች ዕጸ ፋርስ ለመዝናኛ መፈቀድ አለበት በሚለው ላይ ድምጻቸውን ይሰጣሉ።
በተመሳሳይ በሚሲሲፒ ደግሞ መራጮች ዕጸ ፋርስ ለሕክምና መፈቀድ አለበት ወይስ የለበትም በሚለው ላይ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
አሸናፊውበይፋስራየሚጀምረውመቼነው?
በምርጫው ጆ ባይደን የሚያሸንፉ ከሆነ ወዲያውኑ ወደ ስራ መግባት አይችሉም።
ምክንያቱም አዲሱ ፕሬዝዳንት የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን ለመሾምና እቅድ ለማዘጋጀት የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋቸዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት በይፋ ኃላፊነታቸውን የሚረከቡትና ቃለ መሀላ የሚፈጽሙበት የበአለ ሲመት ቀን ደግሞ ጥር 12 ላይ በዋሽንግተን ዲሲ ካፒቶል ህንጻ ደረጃ ላይ ይካሄዳል።
በመቀጠልም አዲሱ ፕሬዝዳንት ወደ ዋይት ሀውስ በመሄድ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት እዛው ይቆያሉ።












