ኮሮናቫይረስ፡ የስፔን ቀብር አስፈጻሚዎች የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ

በስፔን የሚገኙ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅቶች ሰራተኞች በኮሮረናቫይረስ የሚሞሩ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ የሰራተኛ ቁጥር ይጨመርልን በማለት የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ተሰምቷል።

የሰራተኞች ማህበራት እንደገለጹት ወረርሽኙ መጀመሪያ ላይ በአገሪቱ ሲከሰት ቀብር አስፈጻሚዎቹ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው የአንዳንድ ሰዎችን ቀብር ሳይፈልጉ እንዲያራዝሙ ተገድደዋል።

በአሁኑ ሰአት ደግሞ አውሮፓ በሁለተኛ ዙር የቫይረሱ ስርጭት እየተፈተነች ትገኛለች።

በርካታ አገራት ቫይረሱ እንደ አዲስ መሰራጨት መጀመሩን ተከትሎ የሰአት እላፊዎችና የእንቅስቃሴ ገደቦችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሞከሩ ሲሆን የሟቾችም ቁጥር ቢሆን እያንሰራራ መጥቷል።

ቅዳሜ ዕለት ኦስትሪያ እና ፖርቹጋል አዳዲስ መመሪያዎችን ማስተዋወቃቸው ይታወሳል።

በመላው ስፔን የሚገኙ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅቶች ሰራተኞች ዕሁድ ዕለት አድማውን መትተዋል። አድማው የተካሄደው ደግሞ ፈረንሳያውያን የሞቱባቸውን ሰዎች መቃብር ስፍራ በሚጎበኙበት ቀን ነው።

አንድ በዋና ከተማዋ ማድሪድ የሚገኝ የቀብር አስፈጻሚ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ሲናገር በአሁኑ ሰአት እየጨመረ የመጣውን የሟቾች ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ15 እስከ 20 ሰራተኞች እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አርብ ዕለት ብቻ በስፔን 239 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ የበርካታ ሰዎች አስክሬን ሳይቀበር ለተጨማሪ አንድ ሳምንት እንዲቆዩ የተገደዱ ሲሆን የቀብር ስነስርአቱም ቢሆን ከከተማዎች አካባቢ ራቅ ባሉ ቦታዎች ነበር የሚካሄደው።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ስፔን እስካሁን ከ1.1 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ያስታወቀች ሲሆን 35 ሺ 800 ደግሞ የሟቾች ቁጥር ነው።

በሌሎች የአውሮፓ አገራትም ቢሆን የሁለተኛ ዙር ስርጭቱን ተከትሎ በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። ፈረንሳይ ባለፉት 24 ሰአታት ብቻ 46 ሺ 290 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የገለጸች ሲሆን ትናንት ከትናንት በስቲያ ደግሞ 35 ሺ 641 ሰዎች መያዛቸውን አስታውቃ ነበር።

በአጠቃላይ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 37 ሺ 19 ደርሷል።

ጣልያን ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር አዳዲስና ውጤታማ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሪያለው ብላለች። የአገሪቱ የጤና ሚኒስትሩ ሮቤርቶ ስፔራንዛ በጣልያን ያለውን ስርጭት ለመቆጣጠር ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴን መገደብ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።