የአሜሪካ ምርጫ የሕዳሴ ግድብ ፖለቲካን እንዴት ሊቀይር ይችላል?

የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ሊካሄድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ እና ዲሞክራቱ ጆ ባይደን የሚያደርጉትን የምረጡኝ ዘመቻቸውም እያጠናቀቁ ይገኛሉ። ወደ 70 ሚሊዮን የሚጠጉ አሜሪካውያንም ድምጻቸውን ሰጥተዋል።
ይህን የአሜሪካ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሜሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ መላው ዓለም በአትኩሮት የሚመለከተው ጉዳይ ነው።
የዚህ የምርጫ ውጤትም መጠን እና ስፋቱ ይለያይ እንጂ በሕዳሴ ግድብ ፖለቲካ ላይ ተጽእኖ ሊያመጣ እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።
አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት አላቸው።
አሜሪካ "በሽብር" ላይ ከፍታ በነበረው ጦርነት በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ አንዷ ትልቋ አጋር ኢትዮጵያ ሆና ቆይታለች።
ይሁን እንጂ በቅርቡ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ካለችው የኃይል ማመንጫ ግድብ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከምታደርገው ድጋፍ 130 ሚሊዮን ዶላር መከልከሏ ይታወሳል። በግድቡ ጉዳይም አሜሪካ ለግብጽ ወግና ቆማለች። ይህንንም ፕሬዚደንት ትራምፕ በአደባባይ አንጸባርቀዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ግብጽ የሕዳሴ ግድቡን "ልታፈነዳው ትችላለች" ሲሉ ተደምጠዋል። ለመሆኑ የምርጫው ውጤት በሕዳሴ ግድብ ፖለቲካ ላይ የሚኖረው ለውጥ ምንድነው?
'አሜሪካ ግብጽን ትታ ለኢትዮጵያ አትወግንም'
በዩናትድ ኪንግደም በሚገኘው ኪል ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አወል አሎ (ዶ/ር) ሪፐብሊካኖቹም ይሁኑ ዲሞክራቶች ምርጫውን ቢያሸንፉ የነበረውን የአሜሪካ የውጪ ፖሊስ የሚያስቀጥሉት ይላሉ።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊስ ሁልጊዜም ቢሆን በአገሪቱ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን በማስታወስ የምርጫው ውጤት በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል የቆየውን ግነኙነት ያን ያህል ሊቀይር እንደማይችል ይናገራሉ።
የተለየ የሚያደርገው "ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም አቀፍ ሕግ እና ስምምነቶች ተገዢ የሚሆኑ ሰው አይደሉም የሕዝቡን ትኩረት ለማግኘት ከእርሳቸው የማይጠበቅ ንግግር ይናገራሉ" ይላሉ።
ትራምፕ አንዳንድ ጊዜ እንደ ፕሬዚዳንት ሳይሆን "ልክ እንደ ሰባት ዓመት ልጅ ይናገራሉ" ይላሉ።
ስለ ሕዳሴ ግድብ በቅርቡ የተናገሩትም ለዚሁ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አወል አሎ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።
ቀድሞውንም ቢሆን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አሜሪካ ግብጽን ገሸሽ አድርጋ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ ታዞራለች ብሎ ማሰቡ ስህተት መሆኑንም ጠቆም ያደርጋሉ።
አሜሪካ በመካለኛው ምስራቅ አገራት ልዩ ፍላጎቶች እንዳላት የሚያስረዱት አዎል (ዶ/ር) ከእነዚህም መካከል ዋነኛው የእስራኤልን ፍላጎት ማስጠበቅ ነው ይላሉ።
ለአሜሪካ ሁነኛ ወዳጅ ለሆነችው እስራኤል ደግሞ እውቅና እና ድጋፍ ስታደርግ የቆየችው ተጽእኖ ፈጣሪ የአረብ አገር ግብጽ መሆኗንም ያወሳሉ።
ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ከደረሱ እና ለእስራኤል እውቅና ከሰጡ ጥቂት የአረብ አገራት መካከል አንዷ ግብጽ መሆኗ ይታወቃል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ "ትራምፕ ፒስ ፕላን" በተባለው እቅዳቸው ለእስራኤል እና ፍልስጥኤም ግጭት መፍትሄ ያሉትን አማራጭ እየተገበሩ ይገኛሉ።
በቅርቡም የተባበበሩት ዩናይትድ አረብ ኤምሬት እና ባህሬን ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ደርሰዋል። ጎረቤት አገር ሱዳንም ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ለመፈረም በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
አዎል አሎ (ዶ/ር) ፕሬዚዳንት ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈው ለሁለተኛ ዙር የሰልጣን ዘመን በዋይት ሃውስ የሚቆዩ ከሆነ በዚሁ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲያቸው የሚቀጥሉ ይሆናል ይላሉ።
ዲሞክራቶችም ቢሆኑ ይህን ምርጫ ቢያሸንፉ በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ ቁልፍ ነገር ስለሆነ ለኢትዮጵያ ለውጥ ይዞ እንደማይመጣም ይገልፃሉ።
ይሁን እንጂ ጆ ባይደን ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ቢመረጡ ጉዳዩን ትራምፕ እየሄዱበት ባለው መንገድ ሳይሆን የሚያስቀጥሉት ዓለም አቀፍ ሕግ እና ስምምነቶችን ተከትሎ እንደሚሆንም ያስረዳሉ።
የትራምፕ አስተዳደር ያቋረጠውን የገንዘብ እርዳታም ጆ ባይደን ሊያስቀጥሉ እንደሚችሉ በመጠቆም ይሁን እንጂ የጆ ባይደን አስተዳደርም ግብጽን ትቶ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ ያዞራል ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም ይላሉ።
በሌሎች አገራት ላይ ግን የምርጫ ውጤት ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ለኢትዮጵያ ዲሞክራቶች ወይስ ሪፐብሊካን . . . ?
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ብርሃኔ ቤካ የዋሺንግተን ዲሲ ነዋሪ ሰትሆን ከዲሞክራት ፓርቲ ጋር አብራ እንደምትሰራ ትናገራለች። ብርሃኔ፤ "ሰልጣን መልሰን ለመያዝ ትልቅ ቅስቀሳ እያደረግን ነው" ትላለች።
ብርሃኔ የመምረጥ መብት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዲሞክራት እጩዎች ድምጻቸውን እንዲሰጡ ቅስቀሳ እያደረጉ መሁኑን በመጥቀስ አብዛኛው የመምረጥ መብት ያለው ስደተኛ ድጋፉን እየገለጸ ያለው ለጆ ባይደን ፓርቲ ነው ትላለች።
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዲሞክራቱ ባራክ ኦባማ ለሥራ ጉብኝነት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አስታውሳ ዲሞክራቶች ምርጫውን ቢያሸንፉ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የተሻለ ግንኙነት እንደሚኖራቸው ትናገራለች።
ሌላኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊት እና ከአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጋር አብራ የምትሰራው ሴና ጂምጂሞ ይህ የአሜሪካ ምርጫ ለአሜሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ወሳኝነት አለው ትላለች።
ሴና ዲሞክራቶች በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋርም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ግነኙነት ነበራት ትላለች።
የትራምፕ አስተዳደር ለሁለተኛ ዙር በስልጣን እንዲቆይ እድሉን የሚያገኝ ከሆነ ኢትዮጵያ እየገነባች ባለችው ግድብ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ታስረዳለች።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጥቅምት 24 ይካሄዳል።












