አሜሪካ ከ70 አመታት በኋላ በፌደራል ደረጃ አንዲት ሴትን በሞት ልትቀጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ ከ70 አመታት በኋላ የፌደራል እስረኛን በሞት ልትቀጣ መሆኑን የፍትህ ዲፓርትመንቱ አስታውቋል።
የሞት ብያኔ የተወሰነባት ግለሰብ ሊዛ ሞንቶጎመሪ ትባላለች።
ሊዛ፣ በጎሮጎሳውያኑ 2004 ከሞንቶጎነመሪ ወደ ካንሳስ፣ ሚዞሪ ግዛት ቡችላ ለመግዛት ጆ ስቲኔት የተባለች ግለሰብ ቤት ሄደች።
ሊዛ ግለሰቧ ቤት ከገባች በኋላ ጆ ስቲኔትን አንቃ መሬት ላይ ጣለቻት። ጆ ስቲኔት በወቅቱ የስምንት ወር ነፍሰ ጡርና ለመውለድም ተቃርባ ነበር ተብሏል።
ጆ ስቲኔት ራሷን በሳተችበት ወቅትም ሊዛ ሆዷን በቢላዋ ቀዳ ልጁን ለማውጣት ስትሞክር ጆ ነቃች።
ሊዛም ጆን ከገደለቻት በኋላ ህፃኑን ይዛ ሄዳለች። የራሷም ልጅ እንደሆነ ለሰዎች ትናገር ነበር ተብሏል።
በ2007ም የሞንቶጎመሪ ፍርድ ቤት በግድያና ህፃን በማገት ወንጀል የሞት ቅጣት ወሰነባት።
በወቅቱ ጠበቆቿም ህፃን እያለች በደረሰባት ከፍተኛ ድብደባ የተወሰነ የአዕምሮ ክፍሏ እንደተጎዳና ይህም ሁኔታ የአዕምሮ ህመም ስላስከተለባት ሞት አይገባትም ብለው ተከላክለው ነበር።
ሆኖም ክርክራቸው ተቀባይነት አላገኘም።
የሞት ብያኔውም የሚፈፀምባት ከሁለት ወራት በኋላ በኢንዲያና ግዛት ነው። ቅጣቱም ተፈፃሚ የሚሆነው በመርፌ ነው።
በፌደራል ደረጃ የአሜሪካ መንግሥት በሞት የቀጣት ቦኒ ሄዲ የምትባል ግለሰብ ስትሆን ወቅቱም በጎሮጎሳውያኑ 1953 እንደሆነም ከሞት ቅጣት መረጃ ማዕከል የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ሌላኛው በፌደራል ደረጃ የሞት ቅጣት የተላለፈበት ብራንደን በርናርድ የተባለው ግለሰብ እንዲሁ ታህሳስ ላይ ውሳኔው ተፈፃሚ ይሆንበታል።
ግለሰቡ ሁለት ወጣት የሃይማኖት ልዑካንን በ1999 በመግደል ወንጀል ነው ተጠያቂ የሆነው።
የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፕሬዚዳንት ጄኔራል ዊልያም ባር እንዳሉት እነዚህ ወንጀሎች የሰው ልጅ ማሰብ ከሚችላቸው በላይ "በአሰቃቂ ሁኔታ የተፈፀሙ ግድያዎች ናቸው" በማለት ተናግረዋል።
ባለፈው አመት የትራምፕ አስተዳደር በፌደራል ደረጃ የሚፈፀሙ የሞት ቅጣቶች አንደሚመለሱ አስታውቋል።












