በቫቲካን ሁለት የካቶሊክ ቄሶች በወሲባዊ ጥቃት ክስ ተመሰረተባቸው

የቫቲካን ፍርድ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሁለት የካቶሊክ ቄሶች አንድ ታዳጊ ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ በቫቲካን ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አመራር መቀመጫ የሆነችው ቫቲካን በቄሶች ላይ ክስ ስትመሰርት የመጀመሪያውም ነው ተብሏል።

የ28 አመቱ ቄስ ገብርኤል ማርቲኔሊ በቤተክርስቲያኑ ያገለግል የነበረ ታዳጊ ለአምስት አመታት ያህል በጎሮጎሳውያኑ 2007-2012 ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈፀም ተከሰዋል።

ታዳጊው ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተጨማሪ የመንፈሳዊ ትምህርትም ይከታተል ነበር ተብሏል።

ቄስ ገብርኤል የስነ መለኮት ተማሪና ዲያቆን በነበሩበት ወቅት ነው የ13 አመቱ ልጅ ላይ ጥቃት ማድረስ የጀመሩት።

ሌላኛው የ72 አመቱ ቄስ ኤንሪኮ ራዲስ የስነ መለኮት ትምህርት ቤቱን በበላይነት ይቆጣጠሩ የነበረ ሲሆን ተፈፀመ የተባለውን ወሲባዊ ጥቃትም ሸፍነዋል በሚልም ነው ክስ የቀረበባቸው።

ቄስ ኤንሪኮ ሁኔታውን እያወቁም ቄስ ገብርኤል የቅስና ማዕረግ ሲሰጣቸው ነገሩን ሸፋፍነዋልም ተብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ይፋዊ የሆነ ምርመራም እንዳይካሄድ እክል መፍጠራቸውም ተገልጿል።

የወሲባዊ ጥቃቱ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኗ ቢታወቅም ይፋ የሆነው ጋዜጠኞች ተጠቂውን ከሶስት አመታት በፊት ማናገራቸውን ተከትሎ ነው።

ሁለቱም ቄሶች ይግባኝም አልጠየቁም፤ በክሳቸውም ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በአለም ላይ በርካታ የካቶሊክ ቄሶች በወሲባዊ ጥቃት ተወንጅለው ክስ የተመሰረተባቸው ቢሆንም ቫቲካን ግን በግዛቷ ላይ ክስ ተመስርቶ አያውቅም።

በትናንትናው ዕለት የተጀመረው የፍርድ ሂደትም ቫቲካን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አመራር መቀመጫ ከመሆኗም አንፃር ታሪካዊ ነው ተብሏል።

የፍርድ ሂደቱ ለሁለት ሳምንት ቀጠሮ በመስጠትም ተጠናቋል።