ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ቫይታሚን ዲ ከኮቪድ-19 ይከላከለን ይሆን?
ተመራማሪዎች ቫይታሚን ዲ ሰውነታችን የበሽታ መከላከል ስርዓት ብርታትን በመስጠት ከኮቪድ-19 ጋር ለሚያደርገው ፍልሚያ እገዛ ያደርጋል ወይ? የሚለውን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ሙከራ ለማድረግ በጎ ፈቃደኞችን እየፈለጉ መሆኑ ተገልጿል።
በጎ ፈቃደኞቹ ከጸሀይ ብርሀን የሚገኘው ቫይታሚን ዲ እጥረት ካለባቸው ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት በፖስታ ቤት በኩል የቫይታሚን ዲ እንክብሎች ወደቤታቸው ይላክላቸዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎችና ነዋሪዎች ደግሞ የብርዱ ወቅት እየመጣ መሆኑን ተከትሎ የቫይታሚን ዲ እጥረት በሰውነታችሁ ውስጥ ሊፈጠር ስለሚችል እንክብሎቹን ብትወስዱ ጥሩ ነው ተብለዋል።
የቫይታሚን ዲ እንክብሎቹ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በሽታ የመከላከል አቅምን ከፍ ለማድረግና ኢንፌክሽኖችን ለመቀነስም በእጅጉ ጠቃሚ ነው ተብሏል።
የቫይታሚን ዲ እጥረት የሚታይባቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ እድሜያቸው የገፋና የአፍሪካ አልያም የእሲያ ዝርያ ያለባቸው ሰዎች ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች ለኮቪድ-19 ተጋላጭ መሆናቸውም ሌላ አሳሳቢ ነገር ነው።
በለንደን ኩዊን ሜሪ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እየተደረገ የሚገኘው ምርምር በባርትስ በጎ አድራጎት ድጋፍ ይደረግለታል። በምርምሩም የቫይታሚን ዲ እንክብሎች ለሰዎች ይታደላሉ።
የምርምሩ መሪ የሆኑት ዴቪድ ጆሊፍ እንደሚሉት ''ሙከራው በዚህ ረገድ ጠንከር ያለ ምላሽ ይሰጠናል ብለን እናምናለን'' ብለዋል። አክለውም ''ቫይታሚን ዲ ኮቪድ-19ኝን የመከላከል አቅም ከፍ የሚያደርግ ከሆነ ትልቅ ዜና ይሆናል'' ብለዋል።
''የቫይታሚን ዲ እንክብሎች እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ የሚገኙ ናቸው፤ በተጨማሪም የጎንዮሽ ጉዳታቸው ዝቅተኛና በቀላሉ መገኘት የሚችሉ ናቸው። ወረርሽኙን ለመዋጋት እየተሰራ ያለው ዓለማ አቀፍ ሰራ በደንብ ሊያግዝ ይችላል''
ምንም እንኳን የቫይታሚን ዲ እንክብሎችን መውሰድ ለጤና ጠቃሚ ቢሆንም ከህክምና ባለሙያዎች ምክር ውጪ መውሰድ ግን የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።