ኮቪድ-19፡ ፕሬዚደንት ትራምፕ በኮቪድ-19 በተያዙ ከቀናት በኋላ ወደ ሥራ መመለሳቸው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ በተያዙ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው መግለጫ መስጠታቸው ተገለፀ።
ፕሬዚደንቱ ለ24 ሰዓታት ያህል የኮቪድ-19 ምልክት ያልታየባቸው ሲሆን ለተከታታይ አራት ቀናትም ትኩሳት እንዳልነበራቸው የግል ሐኪማቸው ሴን ኮንሊይ ተናግረዋል።
ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ደህንነት ይሰማቸው እንደነበር ገልፀው፤ "ይህ በፈጣሪ መባረክ ነው" ብለዋል።
በንግግራቸውም ሁሉም አሜሪካዊያን ለእርሳቸው የተሰጠውን መድሃኒት እንዲያገኙ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በመሆኑም በመድሃኒት አምራቹ ሬጀኔሮን የተመረተውን መድሃኒት በነፃ ለመስጠት ፕሬዚደንቱ ቃል ገብተዋል።
ፕሬዚደንቱ አክለውም ባለፈው ሳምንት የተሰጣቸው በሙከራ ላይ ያለው የሰውነት በሽታ መከላከል አቅምን የሚጨምረው አንቲቦዲ ማገገሚያ ብቻ ሳይሆን ፈዋሽ ነው በማለትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠር መጠን [ዶዝ] ያለው መድሃኒት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።
ይሁን እንጅ ድርጅቱ የሚያመርተው መድሃኒት በፌደራል የመድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የተረጋገጠ አይደለም።
"ይህ መባረክ ነው፤ ስለዚህ መድሃኒት ሰምቼ ነበር፤ እንድወስደው ጠየቅኳቸው፤ በጣም አስገራሚ ነበር" በማለትም ለድንገተኛ ህመም መድሃኒቱን ለመጠቀም ፈቃድ ለማግኘት እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቱ ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ ወደ ቻይና ጣት ወደ መቀሰራቸውም ተመልሰዋል።
"ለመድሃኒቱ አትከፍሉም። ይህ ለመፈጠሩ የእናንተ ስህተት የለበትም። ይህ የቻይና ጥፋት ነው። ለዚህም ቻይና ትልቅ ዋጋ ትከፍላለች። ይህ የቻይና ጥፋት ነው" ብለዋል።
ቀደም ብሎ ዶ/ር ኮንሊ ፕሬዚደንቱ በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል ከገቡበት አንስቶ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ እንዳልተገጠመላቸውን፣ ኦክስጅን እንዳላስፈለጋቸው ተናግረዋል።
የትራምፕ ደጋፊዎች ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ ጥሩ አመራር ማሳየታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ ተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ የፕሬዚደንቱ ባህሪ አለመጨበጥ እየባሰበት ነው ሲሉ ተችተዋል።
ፕሬዚደንቱ ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ እና ሌላ ረዳታቸው በበሽታው መያዛቸው ከተሰማ በኋላ ዋይት ሃውስ አዲስ የጥንቃቄ መመሪያዎችን አስቀምጧል።
የአገሪቱ ፕሬዚደንታዊ ምረጫ እአአ.ኅዳር 3 ይካሄዳል። ከምርጫው በፊት በኮሮናቫይረስ የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ ተነስቷል። ፕሬዚደንቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ማክሰኞ ዕለት ከዴሞክራቶች ጋር የነበራቸውን ውይይት ማብቃቱን ገልፀዋል።
በኋላ ላይ ግን በግላቸው በተወሰኑ እርምጃዎች ላይ ብቻ እንደሚስማሙ ተናግረዋል።












