የትግራይ ክልል፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔና ተግባራዊነቱ

የፎቶው ባለመብት, OFFICE OF THE PM
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ የደረሰ ይመስላል።
በተለይም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ፓርላማው ምርጫው በሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲራዘም ያፀደቀ ቢሆንም የትግራይ ክልል ምርጫ ማድረጉ የበለጠ ነገሩን አክርሮታል።
ምክር ቤቱ ስልጣኑን የሕገ መንግሥት ትርጉም በመስጠት ማራዘሙ ሕገ መንግሥታዊ መሰረት እንደሌለውም የትግራይ ክልል ይጠቅሳል።
የፌደራል መንግሥቱ ደግሞ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ባለው ምርጫም ህወሓት አብላጫ ድምፅ አግኝቶ ሕጋዊ መንግሥት መስርቻለሁ፤ እንዲሁም ዶክተር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤልንም የክልሉ ፕሬዚዳንት አድርጌ ሰይሜያለሁ ብሏል።
ሆኖም በትግራይ ክልል የተካሄደው ስድስተኛ ክልላዊ ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠርና ተፈፃሚ የሌለው ነው በማለትም የፌዴሬሽን ምክርቤት ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህ ሳምንት ደግሞ ህወሓት መስከረም 25/2013 ዓ.ም የፌደራል መንግሥቱ ስልጣን ማብቂያ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ፓርላማው ሕጋዊ ስልጣን የላቸውም በማለት፤ አባላቱ በፌዴሬሽንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ያላቸውን ውክልናና ኃላፊነት እንዲለቁ ጥሪ አቅርቧል።
በምላሹም መስከረም 26/2013 ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ውሳኔ አስተላልፏል።
ምክር ቤቴ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈውም ነሐሴ 30/2012 ዓ.ም አድርጎት በነበረው አስቸኳይ ጉባኤ የትግራይ ክልል ያደረገው ምርጫ እንዳልተደረገና እንደማይፀና ያስተላለፈውን ውሳኔንም በመጣሱ ነው።
ይህንን ውሳኔ በበላይነት ሲከታተል የነበረው የሕገ መንግሥቶች ጉዳዮችና የማንነት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ ክልሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ አላከበረም ማለቱም ተገልጿል።
"የፌደራል መንግሥት የክልሉ ከተማ፣ ወረዳና ቀበሌ አስተዳደሮች ጋር ግንኙነት ማድረግ ያስፈለገው ህጋዊ ናቸው ብሎ ስለሚያምን ነው"
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ ያራዘመውን ውሳኔ በመተላለፍና "ሕገወጥ" ያለውን ምርጫ በማካሄዱም የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካላት ጋር ምንም ግንኙነት ላለማድረግም ውሳኔ ላይ ደርሷል።
በዚህም ውሳኔ መሰረት የፌደራል መንግሥት የትግራይ ሕዝብን የልማትና መሰረታዊ አገልግሎቶች ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ የከተማና፣ ወረዳና ቀበሌ አስተዳደሮችና በክልሉ ከሚገኙ ሕጋዊ ተቋማት ጋር የሥራ ግንኙነት እንደሚያደርግም አስታውቋል።
ይህ ውሳኔ ሲተላለፍ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ያካሄደው ምርጫ "ሕገወጥ" በመሆኑ፤ ምክር ቤቱ የፌደራል መንግሥቱ ተፈፃሚነት የለውም ባለው ምርጫ የክልሉ ምክር ቤትም ሆነ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚዎች በመዋቀራቸው ምክንያት ምንም ግንኙነት እንዳይኖረው ውሳኔ ተላልፏል፤ ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቃለ አቀባይ አቶ ካሳሁን በቀለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ማዕከላዊው መንግሥት ከዚህ በኋላም በቀጣይነት ግንኙነት የሚኖረው ሕዝቡን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
የትግራይ ሕዝብን የሰላምና የልማት መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማዕከልም በማድረግ በክልሉ ከተሞች፣ ወረዳዎችና ቀበሌ አስተዳደሮች ወይም ቃለ አቀባዩ "ሕጋዊ" ካሏቸው ተቋማት ጋር የፌደራል መንግሥቱ በቀጥታ ግንኙነት ያደርጋል ብለዋል።
የፌደራል መንግሥቱ ከነዚህ ተቋማት ጋር በቀጥታ ለመስራትም የመረጠበት ምክንያት የአካባቢ ምርጫ ባለመደረጉና አስተዳደሮቹ በነበሩበት በመቀጠላቸው መሆኑንም አቶ ካሳሁን ያስረዳሉ።
የከተማ አስተዳደሮችም ሆነ ወረዳዎች የሚመሩት በክልሉ አስተዳደር ወይም እውቅና የሚያገኙት በክልሉ ሕገ መንግሥት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌደራሊዝም መምህር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ ይናገራሉ።
ከዚህም አልፎ እነዚህ አስተዳደሮች በክልሉ ማስፈፀሚያ አዋጅም የተደገፉ ናቸው። ከዚህም አንፃር የከተማው፣ የወረዳውም ሆነ የቀበሌ አስተዳደሮችም ሆነ የሚመረጡትም ሆነ ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግሥት ከመሆኑም ጋር ተያይዞም የፌደራል መንግሥቱ ከክልሉ ሕግ አውጪና ሥራ አስፈፃሚ ጋር ግንኙነት የለኝም ብሎ ተጠሪነታቸው ለክልሉ ከሆኑ አካላት ጋር እሰራለሁ የሚለው ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄም መነሳቱ አልቀረም።
ይህንንም ጥያቄ ቢቢሲ ለአቶ ካሳሁን ያቀረበላቸው ሲሆን እሳቸውም ቢሆን በዋነኝነት የሚያነሱት የትግራይ ክልል ያካሄደው የክልል ምክር ቤት ምርጫ "ሕገ መንግሥቱን የጣሰ" መሆኑንና እሱን ተንተርሶ የከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካላት መዋቀሩን ነው።
በአሁኑ ወቅት ክልሉ ያካሄደው ምርጫ ወረዳዎችን፣ ከተማ አስተዳደሮችን ወይም ቀበሌዎችን ባለማካተቱም የፌደራል መንግሥቱ እነዚህን አካላት "ሕገ ወጥ" አይደሉም ብሎ ያምናል ይላሉ።
"ምክር ቤቱ ውሳኔውን ሲወስን ከክልሉ ሕዝብ ሰላም፣ ልማትና መሰረታዊ የአገልግሎት ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ሕዝቡ እንዳይጎዳ የሚል ቀጥታ ግንኙነት በተለያየ መንገድ ሊያረግ ይችላል ማለት ነው። የአካባቢና የወረዳ ምርጫ ስላልተደረገ በነበሩበትረ የቀጠሉ ስለሆነ ከእነሱ ጋር የተጀመረው የሰላምና የልማት ሥራዎች ከሕዝቡ ጋር ይካሄዳሉ" ብለዋል።
የትግራይ ክልል፤ ምክር ቤቱ ምርጫውን ያራዘመው ከሕገ መንግሥቱ ውጪ በሆነ ትርጓሜ ነው በማለት ትችት የሚያቀርብ ሲሆን፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወሰነውንም ውሳኔ ተከትሎ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሩፋኤል ሽፈረ ከ2.7 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የተሳተፈበትን ምርጫ ለሕዝቡ ያለውን ንቀት ያሳየ ብለውታል።
ሚሊዮኖች የተሳተፉበትን ምርጫ ተቀባይነት የለውም ማለት? እንዲሁም የአሁኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ሕዝቡን የመግፋትና ክልሉንም የኢትዮጵያ አካል ሆኖ እንዳይታይ ማድረግ አይሆንም ወይ? የሚሉ አስተያየቶች መሰማታቸውን ጠቅሰን ለአቶ ካሳሁን በጠየቅናቸው ወቅትም ውሳኔው ሕገ መንግሥቱን የማክበር ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ።
ክልሎች የሚያወጧቸው መመሪያዎች፣ ደንቦችና ሕጎች ከሕገ መንግሥቱ በላይ ሊሆኑ እንደማይችሉ በመጥቀስም ምክር ቤቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ሰጥቷል። የሕገ መንግሥቱ ትርጓሜም ተፈፃሚነቱ በሁሉም ምክር ቤቶችና በሁሉም ክልሎች መከበር አለበት በማለት አፅንኦት ይሰጣሉ።
"እኛ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ነው የምንሰራው፤ ሕገ መንግሥት የአንድ ፓርቲ አይደለም፤ የሕዝብ ስለሆነ መከበር አለበት። ጥያቄዎች ካሉ በተለየ አውድ መፈታት ይችላሉ። ሁላችንም ቢሆን ከሕግ በላይ ልንሆን አንችልም፤ አገሪቷ የምትመራበት ሕገ መንግሥት አላት። ይሄንን ደግሞ ሁሉም የማክበር ግዴታ አለበት" ብለዋል አቶ ካሳሁን።
የፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልል ቀጣይ ግንኙነት እንዴት ይከወናል?
ምክር ቤቱ የወሰነው የውሳኔ አፈፃፀምም በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የበላይ አመራሮችና በሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ክትትል ይደረጋልም የሚል ውሳኔም ተላልፏል።
አፈፃፀሙን የሚወስነው ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮም መሆኑን ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) ይጠቅሳሉ።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት ባለው የስልጣን አወቃቀርና ተዋረድ መሰረት የፌደራል መንግሥቱ ቀጥታ ግንኙነት የሚያደርገው ከክልሎች ወይም ከክልል መንግሥታት ሕግ አውጪና አስፈፃሚ ጋር ነው። የአሁኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ይህንን ግንኙነት የቀየረ እንደሆነ ሲሳይ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነሐሴ 30/2012 ዓ.ም ባደረገው የአስቸኳይ ጉባኤ ክልሉ ያደረገው ስድስተኛ ክልላዊ ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠርና ተፈፃሚ የማይሆን ነው በማለትም ውሳኔ አስተላልፏል።
በወቅቱም ግንኙነታቸው ሊቋረጥ የሚችል መሆኑንም ያመላከተበት ውሳኔም መሆኑን የሚገልፁት ሲሳይ (ዶ/ር) ከክልሉ የሕግ አውጭው ምክር ቤትና አስፈፃሚው ጋር ግንኙነት እንዲቋረጥ የወሰነበትም የዚያ ቀጣይ ተግባራዊ ውሳኔ ነው።
በዚህም መሰረት የአሁኑ ውሳኔ በተለያየ ደረጃ ያሉት የፌደራል የመንግሥት አካላት ከትግራይ ክልል የሕግ አውጪው ምክር ቤትና አስፈፃሚው ጋር ግንኙነት እንዳያደርግ የደነገገ መሆኑንም ያስረዳሉ።
ከዚህ በኋላ የፌደራል መንግሥት በክልሉ ውስጥ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ የሚሰራቸውን መሰረተ ልማት ተግባራት ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከወረዳና ከቀበሌዎች ጋር በቀጥታ ይሰራል ማለትም መሆኑን የውሳኔውን አንድምታ ሲሳይ (ዶ/ር) ይገልፃሉ።
"ከዚህ ቀደም እንደነበረው ከክልሉ መንግሥት አመራር፣ በክልሉ በኩል አድርጎ ወደ ከተማና ወረዳ አስተዳደሮች እንዲወርድ ማድረጉን ትቶ በቀጥታ ራሱ የሚገናኝበት፣ ራሱ አቅርቦቱን የሚሰራበትና ግንኙነቱም ከእነሱ ጋር የሚሆንበት ነው" ይላሉ።
ሆኖም የፌደራል መንግሥቱ በዚህ መንገድ እሰራለሁ ማለቱ ፈታኝ እንደሆነ የሚያስረዱት ሲሳይ (ዶ/ር)፤ ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱት ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚመሩትም በክልሉ አስተዳደር፣ የሚደገፉት በክልሉ ማስፈፀሚያ አዋጅ እንዲሁም እውቅና የሚያገኙት በክልሉ ሕገ መንግሥት በመሆኑ ነው።
የፌደራል መንግሥት ግንኙነቴ ከክልሉ የከተማ አስተዳደሮች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ነው ብሎ ሲወስን እነዚህን ተቋማት ለሁለት አካላት ተጠሪ ያደርጋቸዋል ማለትም እንደሆነ ይናገራሉ።
ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት ይቋረጣል ሲባልም የበጀት ድጋፉን ጭምር ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑንም ሲሳይ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።
በትናንትናው ዕለትም የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚው አካል ሕጋዊ ሰውነት የላቸውም በሚል የፌደራል መንግሥት የበጀት ድጎማ እንደማይደረግ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
ከዚህ ቀደም የፌደራል መንግሥት ለክልሉ መንግሥት ሲሳይ (ዶ/ር) እንደሚሉት "ፍሎው ግራንት" (ጥቅል ድጋፍ) የሚባል አይነት ነበር የሚሰጠው።
ከዚህ በኋላ ግን እያንዳንዱ በጀት ተከፋፍሎ ለከተማ አስተዳደሮችና ለወረዳዎች ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በሚሆን መልኩ የሚደርስበት አሰራር ውኔው ታሳቢ እንዳደረገም ይጠቅሳሉ። ይህም ማለት ለክልሉ መንግሥት ይላክ የነበረው በጀት በቀጥታ አይላክም ማለትም ነው።
ሲሳይ (ዶ/ር) ይህንን ለማብራራት እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት ፍርድ ቤቶችን ነው። ፍርድ ቤቶች በምርጫ ስለማይደራጁና ቀጣይነት ያለው ሥራ ስለሚሰሩ የፌደራሉ መንግሥት ግንኙነት ከክልሉ ጋር ይሆናል። በዚህም ወቅት የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር ግንኙነት ይኖረዋል።
የበጀት ድጋፍ የሚደረግም ከሆነ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊደረግ የሚችል ቢሆንም፤ ከዚያ ውጭ ግን ከክልሉ ምክር ቤትና ከክልሉ አስፈፃሚ ጋር የሚኖር የበጀትም ይሁን የሥራ ግንኙነት ይቋረጣል።
ከዚህም በተጨማሪ ሲሳይ (ዶ/ር) እንደሚሉት በፌደራሉና በክልሉ ምክር ቤት የስብሰባም ይሁን የስልጠና ግንኙነት አይደረግም።
"የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ተነጋግረውና ተወያይተው መፍትሄ ሊያመጡ ይገባል"
የፌደራሉና የክልሉ መንግሥት እንዲህ ግንኙነት በማይኖርበት ሁኔታ የወደፊቱ የክልሉ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄ ውስጥ መግባቱንም በርካቶች ይናገራሉ። የሁለቱ መንግሥታት እንዲህ ሆድና ጀርባ ሆኖ መሻከር የክልሉ ነዋሪስ እንዴት ይመለከተዋል? የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔስ እንዴት ይታያል?
በመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆነውና የሕግ ባለሙያው ሃብቶም ግርማይ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ የሕግ መሰረት የለውም በማለት ይናገራል።
ከዚህም ባለፈም "ከትግራይ መንግሥት (ባለስልጣናት) ግንኙነት የለኝም ማለቱ በጣም የሚያስቅ ነው። ምክንያቱም ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ነች። ለኢትዮጵያ አንድ ፌዴሬሽን ነች። ብሔርና ብሔረሰቦችን የያዘ ክልል ነው፤ ሦስት ቋንቋዎች የሚናገሩባትን ክልል ጠቅልሎ ከክልሉ መንግሥት ጋር ግንኙነት የለኝም ማለት የሚገርምና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሆነ ይመስለኛል" ብሏል።
እንዲህ አይነት ውሳኔ መተላለፉም ሕዝቡን የበለጠ ሌላ ስሜት ውስጥ የሚያስገባ ነውም ሲል ስጋቱን ይገልጻል።
የእድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው ነገሩ ከቁጭትና ከንዴት ጋር ተያይዞ የሚነገር እንደሆነና ሁለቱም ወገኖች ሰከን ብለው እንደሚያስቡም ተስፋ አድርገዋል።
"አንዳንድ ጊዜ ከቁጭት ከንዴት የሚነገር ነገር አለ። ግን ሲውል ሲያድር ደግሞ ረጋ ብሎ ማሰብ ስላለ ምናልባት ዛሬ የተነገረው ነገር ወደኋላ መለስ ብለው ያስባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።
አገርም ሆነ ሕዝብ መምራት ቀላል እንዳልሆነ በማስታወስም "አገር እየተመራ እንደዚህ አይነት ውሳኔ ማስተላለፍ አይገባም። አገር የሚመራው በመቻቻል፣ በመረዳዳት፣ በመተጋገዝ ነው። ግጭትና ጦርነት ለሁሉም አይበጅም፤ ለሁሉም አያዋጣም፤ ለአገሪቱም ለሕዝቡም አያዋጣምና መለስ ብሎና ረጋ ብለው እንዲያስቡ ነው ማሳሰብ የምወደው" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም አገሪቷ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያደረገቻቸውን ጦርነቶችም ሆነ እንዲሁ በአገር ውስጥ የነበሩ ግጭቶችን በመጥቀስ ትምህርት መውሰድ ይገባል ይላሉ የመቀለው ነዋሪ አቶ ገብረ እግዚአብሔር።
"ይሄ ሁሉ አልፎ ወደ ድርድር መጥተን ሰላም ማምጣት ነው እንጂ እኔ እበልጣለሁ የሚል ፉክክር ጥሩ ስለማይሆን ረጋ ብለው ያስቡ የሚል መልዕክት አስተላልፋለሁ" ብለዋል።
የኤሌክትሪክ መሃንዲሱም አብዱ መሃመድ በበኩሉ የክልሉ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለውና በምርጫ ማሸነፉን ይናገራል። እንዲህም በሆነበት ሁኔታ የፌደራል መንግሥትና የትግራይ ክልል አመራሮች ተነጋግረውና ተወያይተው መፍትሄ ቢያመጡ፣ የፖለቲካ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ አማራጭም መፍትሄን ያቀርባል።
በዚሁ ከቀጠለ አገሪቱ ወዳልተገባ ትርምስ ልትገባ ትችላለች በማለትም እነ ሶርያና ሌሎች አገሮችን በምሳሌነት በመጥቀስ ከእነሱ መማር እንደሚገባና ሕዝብ ሳይጎዳ የመቀራረብ አስፈላጊነትን ይናገራል።












