እግር ኳስ፡ አምስት ቁልፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

የፎቶው ባለመብት, STAFFORD ONDEGO
ኢትዮጵያ ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ከኒጀር ጋር ለምታደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ተጠርተው ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል አምስት ቁልፍ ተጫዋቾች ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው ተነገረ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ለብሔራዊ ቡድኑ ተጠርተው ከነበሩት 36 ተጫዋቾች መካከል ለቡድኑ ወሳኝ የሆኑት አምስት ተጫዋቾች በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።
አቶ ባህሩ ለውድድሩ 41 ተጫዋቾች መጠራታቸውን አስታውሰው፣ አምስቱ በተለያየ ምክንያት ቡድኑን አለመቀላቀላቸውን አመልክተዋል።
ከአምስቱ መካከል ሁለቱ በአሁን ሰዓት በውጭ አገር በሙከራና በመጫወት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም ሁለት ተጫዋቾች ዘግይተው ቡድኑን መቀላቀላቸውን ገልፀው፤ አንደኛው ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበረበት ጉዳት ምክንያት ቡድኑን መቀላለቀል ያልቸለ መሆኑን ተናግረዋል።
ለእግር ኳስ ቡድኑ አባላት የኮቪድ-19 ምርመራ ከመደረጉ በፊት የልብ ምርመራን ጨምሮ አጠቃላይ የጤና ምርመራ መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው፤ የኮቪድ-19 ምርመራውም ለሁሉም መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ለብሔራዊ ቡድኑ ለተጠሩት ለአጠቃላዩ 36 ተጫዋቾች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎ አምስት ተጫዋቾች ላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል አቶ ባሕሩ።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ተጫዋቾች ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉትን የመለየት ሥራ እየተሰራም መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል።
እነዚህ ቫይረሱ የተገኘባቸው አምስት ተጫዋቾች በአሁኑ ጊዜ በሆቴል ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ መደረጉን በመግለጽ፣ ልምምድ እየሰሩ በቶሎ እንዲያገግሙ ፌዴሬሽኑ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆን አብራርተዋል።
የአምስቱ ተጫዋቾች ውጤት እንደተሰማ በቡድኑ አባላት መካከል ድንጋጤ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት የመጡ ባለሙያዎች ሙያዊ ምክር እንደሰጧቸውም ተገልጿል።
እነዚህ በኮቪድ-19 የተያዙ አምስት ተጫዋቾች ለለይቶ ማቆያነት ፈቃድ ወደ ተሰጣቸው ሆቴሎች ዛሬ፣ ሰኞ፣ እንደሚዛወሩም ኃፊው አክለው ተናግረዋል።
አምስቱ ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው ያስታወሱት አቶ ባሕሩ በቡድኑ ላይ የሥነ ልቦና ጫና ቢኖረውም ቶሎ አገግመው ወደ ቡድኑ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል ብለዋል።
ተጫዋቾቹ ከ14 ቀን ለይቶ ማቆያ በኋላ ለጨዋታው ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚገመት ተናግረው፣ እነዚህን ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ የመቀላቀል ውሳኔ ግን የአሰልጣኙ መሆኑን አስረድተዋል።
ቀሪ የቡድኑ አባላትን ከኮሮናቫይረስ ለመጠበቅ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከኒጀር ጋር የሚኖራት ጨዋታ የሚካሄደው ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም መሆኑ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።
በተያያዘ ዜና ከኮሮናቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ ተቆርጠው የቆዩት ከፍተኛ ሊግ፣ አንደኛ ሊግና የሴቶች ፕሪሚየር ሊግን ኅዳር አጋማሽ ላይ ለመጀመር የእግር ስ ፌዴሬሽኑ አቅዶ ለቡድኖች ማሳወቁንና እነርሱም ዝግጅት ማድረጋቸውን አክለው ተናግረዋል።
ውድድሮቹ የሚካሄዱት በዝግ ስታዲየም መሆኑን ገልፀው በሂደት አማራጮች እየታዩ ደጋፊዎች የሚገቡበት ሁኔታ ይፈቀዳል ብለው እንደሚያስቡ ለቢቢሲ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ተናግረዋል።














